ብአዴን በጉባኤው አገራዊ ለውጡን የሚያስቀጥሉ ወጣት አመራሮችን ይመርጣል ብለን እንጠብቃለን-----የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች

50
ባህር ዳር መስከረም 16/2011 የብሔረ አማራ ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ (ብአዴን) 12ኛ ድርጅታዊ ጉባኤ በአገር አቀፍ ደረጃ የመጣውን ለውጥ ሊያስቀጥሉ የሚችሉ አዲስ ወጣት አመራሮች የሚመረጡበት ይሆናል ብለው እንደሚጠብቁ የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች ገለጹ። ከህብተረሰብ ክፍሎቹ መካከል የባህር ዳር ከተማ ነዋሪ አቶ አንዳርጌ አጥናፉ ለኢዜአ በሰጡት አስተያየት ድርጅቱ ነገ በሚጀምረው ጉባኤ በህዝብ ግፊት የመጣውን ለውጥ የሚያስቀጥሉና የህዝብን ጥቅም በዘላቂነት የሚያስጠብቁ ወጣትና ምሁራን አመራሮችን ይመርጣል ብለው ጠብቀዋል ። "የሚመረጡት አመራሮች ከቡድንተኝነት አስተሳሰብ የተላቀቁ እንደሚሆኑም እምነት አለኝ" ሲሉ ምኞታቸውን ገልፀዋል። ድርጅቱ ወደፊት የሚያመጣቸው አመራሮች ሀገራዊ አንድነትን የሚያረጋግጡ፣ በኢትዮጵያዊነት የማይደራደሩና ሀገሪቱን ከድህነት ለማላቀቅ ሌት ተቀን የሚተጉ ሊሆኑ እንደሚገባም አቶ አንዳርጌ አመላክተዋል። ሌላው የከተማው ነዋሪ አቶ ዘለቀ ፀጋ በበኩላቸው የኦሮሞ ዴሞክራሲ ፓርቲ (ኦዴፓ) ባካሄደው 9ኛው ጉባኤ ባሳለፋቸው ጠንካራ ውሳኔዎች ብአዴን ተሞክሮ በመውሰድ የክልሉንና የሀገሪቱን ልማት የሚያስቀጥሉ አመራሮችን መምረጥ እንደሚኖርበት ጠቁመዋል ። የአመራር ምርጫውም አቅምና ችሎታን መሰረት ያደረገ ብቻ ይሆናል ብለው እንደሚጠብቁም ያላቸውን እምነት ገልፀዋል ። "ድርጅቱ አሁን ካለው አገራዊ ለውጥ ጋር ራሱን አጣጥሞ ለመዝለቅ አርማና ስያሜውን ለመቀየር አስቦ መዘጋጀቱ መልካም ነው"  ብለዋል ። ብአዴን በጉባኤው የህዝቡን አንድነት የማጠናከርና ከድህነትና ኋላቀረነት የማላቀቅ ራእዩን ለማሳካት የሚያስችሉ አቅጣጫዎችን ያስቀምጣል ብለው እንደሚጠብቁም አቶ ዘለቀ አመላክተዋል ። "እኛ ከጉባኤው የምንጠብቀው አብዛኛውን ስራ አጥ ወጣት ወደስራ የሚያስገቡ አመራሮች እንዲመረጡ ነው" ያለው ደግሞ በከተማው በቀን ስራ የሚተዳደረው ወጣት ፀጋየ ይታይ ነው። ድርጅቱ በጉባኤው ሥራ ያጣውን ወጣት ወደ ለውጥ በማስገባት ተጠቃሚ በማድረግ የዜጎች ህይወት እንዲቀየር ሌት ተቀን ሊሰሩ የሚችሉ አመራሮችን ይመርጣል የሚል ተስፋ እንዳለው ገልጿል። ከማዕከላዊ ጎንደር ዞን አለፋ ወረዳ የመጡት ዋና ሳጅን ነጋ አድማሱ በበኩላቸው "የድርጅቱ ነባር አመራሮች ከለውጡ ሂደት ጋር እራሳቸውን የሚፈትሹበትና ለውጡን የሚያራምዱ አዳዲስ አመራሮች ወደ ፊት የሚመጡበት ታሪካዊ ጉባኤ ይሆናል የሚል እምነት አለኝ" ብለዋል ። ድርጅቱ የተጀመረውን አገራዊ ለውጥ ለማራመድ፣ የወከለውን ህዝብ ተጠቃሚ የሚያደርግና ኃላፊነቱን ለመወጣት የሚያስችሉ ውሳኔዎችን ያሳልፋል ብለው እንደሚጠብቁም ሳጅን ነጋ አመላክተዋል ።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም