ዲፕሎማሲያችን ነፃነት፣ እኩልነት እና ፍትሃዊነትን መሰረት ባደረገ መልኩ ተጠናክሮ ይቀጥላል - ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አህመድ

230

አዲስ አበባ (ኢዜአ) ህዳር 6 ቀን 2015 ዲፕሎማሲያችን ነፃነት፣ እኩልነት እና ፍትሃዊነትን መሰረት ባደረገ መልኩ ተጠናክሮ ይቀጥላል ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አህመድ ተናገሩ።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አህመድ በ6ኛው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት 2ኛ ዓመት የስራ ዘመን 4ኛ መደበኛ ስብሰባ ላይ ከህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት ለቀረቡላቸው ጥያቄዎች ማብራሪያና ምላሽ ሰጥተዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በማብራሪያቸው የኢትዮጵያ ዲፕሎማሲ ነፃነት እኩልነት እና ፍትሃዊነት መለያ ባህራያቶቹ መሆናቸውን ገልጸዋል።

ይህም ኢትዮጵያ በጋራ ተጠቃሚነት መርህ ላይ የተመሰረተና በዘመናት መካከል የማይቀያየር ለነፃነት እኩልነት ፍትሃዊነት ቀናዒ የሆነ መርህ እንደምትከተል ማሳያ እንደሆነ ተናግረዋል።

ለአፍሪካ ችግሮች አፍሪካዊ መፍትሔ ሊበጅ ይገባል በሚለው መርህም ኢትዮጵያ ከትናንት እስከ ዛሬ ጸንታ የያዘችው አቋም መሆኑን ተናግረዋል፡፡

ምንም እንኳን በርካታ ችግሮች ቢኖሩም በጋራ ማሸነፍ የሚቻልበትን መፍትሄ መፍጠር እንደሚያስፈልግ ጠቁመዋል።

ኢትዮጵያ ከጎረቤቶቿ ጋር መልካም የሚባል ግንኙነት መፍጠር ላይ ስትሰራ መቆየቷን አንስተው፤ ለአብነትም ከጎረቤት ሱዳን ጋር የማያግባቡ ጉዳዮች በዲፕሎማሲ ጥረት መስመር እንዲይዙ መደረጉን ገልጸዋል።  

ከዚህ አኳያ ባለፉት ጊዜያት ኢትዮጵያ ላይ ሰፊ ዲፕሎማሲ ጫና ለማድረግ ሲሞከር ሱዳን ከኢትዮጵያ ጎን መቆሟን ተናግረዋል።

ጎረቤት አገራትን ጨምሮ አፍሪካውያን የኢትዮጵያን ሰላምና ደህንነት ለማረጋገጥ በተደረገው የሰላም ስምምነት ሂደት ላበረከቱት ድጋፍ ምስጋና አቅርበዋል።

በጋራ ተጠቃሚነት ላይ የተመሰረተው የኢትዮጵያ ዲፕሎማሲያዊ እንቅስቃሴ ተጠናክሮ እንደሚቀጥልም ጠቁመዋል።

በዚህም በተለያዩ የዓለም አገራት የሚገኙ ኢትዮጵያውያን ለአገራቸው አምባሳደር በመሆን በሚችሉት ሁሉ አገራቸውን ማገዝ እንዳለባቸውም ጥሪ አቅርብዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም