በሰሜን ኢትዮጵያ በተካሄደው ጦርነት ጉዳት የደረሰባቸውን ወገኖች በትብብር ማገዝ ይገባል

170

አዲስ አበባ (ኢዜአ) ህዳር 6 ቀን 2015 በሰሜን ኢትዮጵያ በተካሄደው ጦርነት ጉዳት የደረሰባቸውን ወገኖች በትብብር ማገዝ እንደሚገባ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ ተናገሩ።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አህመድ በ6ኛው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት 2ኛ ዓመት የስራ ዘመን 4ኛ መደበኛ ስብሰባ ላይ ከህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት ለቀረቡላቸው ጥያቄዎች ማብራሪያና ምላሽ ሰጥተዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በሰጡት ማብራሪያ በሰሜን ኢትዮጵያ በተካሄደው ጦርነት በርካታ ወገኖች ለችግር መዳረጋቸውን አንስተዋል፡፡

እነዚህን ወገኖች ማገዝ ደግሞ ከሁሉም ኢትዮጵያዊ የሚጠበቅ ወገናዊ ኃላፊነት መሆኑን ተናግረዋል፡፡

የትግራይ ህዝብ ሰላም ፈላጊነቱን ሰራዊቱ ባለበት ሁሉ እያሳየ እንደሆነም ነው ጠቅላይ ሚኒስትሩ ያብራሩት፡፡  

የትግራይ ህዝብ ሰላም ሰፍኖ መብራት፣ ውሃና ሌሎች መሰረተ ልማቶች እንዲሟሉለት በተግባር እየገለጸ መሆኑንም ጨምረው ገልጸዋል፡፡

በድርድሩ የተካሄደው የሰላም ስምምነትም በበጎ የሚታይና ለስኬቱም ድጋፍ ማድረግ እንደሚያስፈልግ አንስተዋል።

በጦርነት የተጎዱ አካባቢዎችን ለመደገፍ፣ ለመገንባትና የተፈናቀሉ ወገኖችን ወደ ቀያቸው ለመመለስ እየተሰራ መሆኑንም ገልጸዋል።

ለአብነትም ሰቆጣና አላማጣ ከተሞች መብራት ማግኘታቸውንና ከትግራይ ክልል የተለያዩ አካባቢዎች ተፈናቅለው በሽሬ ከተማ ተጠልለው የነበሩ ወገኖችን የመከላከያ ሰራዊት ወደ ቀያቸው መመለሱን ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም