አሸባሪው ሸኔ ዓላማ የሌለውና ሰላማዊ ዜጎች ላይ ጥቃት በመፈጸም የህዝብ ጠላት መሆኑን በተግባር ያረጋገጠ ቡድን ነው

127

አዲስ አበባ (ኢዜአ) ህዳር 6 ቀን 2015 አሸባሪው ሸኔ ዓላማ የሌለውና ሰላማዊ ዜጎች ላይ ጥቃት በመፈጸም የህዝብ ጠላት መሆኑን በተግባር ያረጋገጠ ቡድን መሆኑን ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ ተናገሩ።

መንግስት የዜጎቹን ደህንነት ለማስጠበቅ የሚወስደውን እርምጃ አጠናክሮ አንደሚቀጥልም ነው የተናገሩት፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ በ6ኛው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት 2ኛ ዓመት የስራ ዘመን 4ኛ መደበኛ ስብሰባ ላይ ከህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት ለቀረቡላቸው ጥያቄዎች ማብራሪያና ምላሽ ሰጥተዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አህመድ አሸባሪው ሸኔን በሚመለከት በሰጡት ምላሽና ማብራሪያ በሽብር ድርጊት የሚገኝ ነፃነት፣ ዴሞክራሲም ሆነ ክብር እንደሌለ ገልጸዋል።

በሽብር መንገድ ዘላቂ ጥቅም ማስከበርም ሆነ ዓላማን ማሳካት እንደማይቻልም ነው የተናገሩት፡፡

የሸኔ ሽብር ቡድን የማይጨበጥና ፍላጎቱም የማይታወቅ ስርዓት የሌለው ኃይል መሆኑንም አብራርተዋል፡፡

ወጥ የሆነ የኮማንድ ስርዓት ከሌለው ኃይል ጋር ተነጋግሮ ችግርን መፍታት በእጅጉን አስቸጋሪ መሆኑም ተናግረዋል።

ከዚህ አኳያ "ለኦሮሞ ህዝብ ጥቅም ቆሜያለሁ" የሚለው አሸባሪው ሸኔ በኦሮሚያ ክልል ሰላማዊ ዜጎችን በመግደል፣ ሃብታቸውን በመዝረፍ እንዲሁም ህዝብ የሚገለገልባቸውን ተቋማት በማውደም የህዝብ ጠላት መሆኑን በተግባር አሳይቷል ነው ያሉት፡፡

በዚህ መንገድ የሚመጣ ሰላምና ነፃነት እንደሌለ ጠቅሰው መንግስትም ከንግግር ውጭ በኃይልና በትጥቅ ትግል የሚገኝም ሆነ የሚሳካ ፍላጎት እንደሌለ ሲያሳውቅ መቆየቱን ጠቅሰዋል።

ንጹሃን ወገኖችን በመግደል፣ ንብረት በማቃጠልና በመዝረፍ የሚገኝ ምንም አይነት ትርፍ እንደሌለም አጽንኦት ሰጥተዋል።

መንግስት ሰላም የማስከበር ግዴታ እንዳለበት ጠቁመው፤ ከዚህ አኳያ ሰላም ለማስከበር የጀመረውን ስራ አጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል፡፡

መንግስት ህግን በማክበር ለሚንቀሳቀስ ማንኛውም ሃይል ለሰላም ቅድሚያ በመስጠት ለመወያየት ዝግጁ መሆኑንም አረጋግጠዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም