የብሔራዊ መታወቂያ አገልግሎት በአስገዳጅነት እንዲሰጥ የሚያደርግ የህግ ድንጋጌ እንዲኖር ተጠየቀ

181

 ህዳር 5/2015 (ኢዜአ)  ብሔራዊ የዲጂታል መታወቂያ አገልግሎት በፈቃደኝነት ብቻ ሳይሆን በአስገዳጅነት እንዲሰጥ የሚያደርግ ድንጋጌ በአዋጅ ሊካተት እንደሚገባ ተጠየቀ ።

የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የህግ፣የፍትህና ዲሞክራሲያዊ ጉዳዮች ከቋሚ ኮሚቴ በብሔራዊ የዲጂታል መታወቂያ ረቂቅ አዋጅ ላይ ከባለድርሻ አካላት የግብዓት ማሰባሰቢያ ውይይት አካሂዷል።

የውይይቱ ተሳታፊዎች በረቂቅ አዋጁ ዜጎች በፍቃደኝነት መመዝገብ ይችላሉ በሚል የተካተተው ሀሳብ በአስገዳጅነት መመዝገብ አላበቸው በሚል እንዲሻሻል ሀሳብ አቅርበዋል።

ምዝገባው ከሌሎች የወሳኝ ኩነት መረጃዎች ጋር በጋራ በተቀናጀ መልኩ መካሄድ እንዳለበትም ነው የጠየቁት።

የዜጎችን የመረጃ ደህንነት በጠበቀ መልኩ መከናወን እንዳለበት ጠቅሰው፤ የመረጃ መዛባት እንዳይኖርም ተጠያቂነት ያለበት አሰራርን የሚፈቅድ ድንጋጌ እንዲኖር ምክረሀሳባቸውን ሰንዝረዋል።

በረቂቅ አዋጁ ሁሉም ዜጎች መመዝገብ አለባቸው በሚል የተካተተው ድንጋጌም በእድሜ ተለይቶ ቢቀመጥ፣ የመታወቂያ አሰጣጡና የሚያበቃበት ጊዜ በግልጽ መደንገግ እንዳለበትም ነው የተነሳው።

ብሔራዊ የዲጂታል መታወቂያው የዜጎችን መረጃ በተደራጀ መልኩ በአንድ ቋት በመያዝ ለአገሪቱ ሁለንተናዊ ዕድገት የበኩሉን ድርሻ የሚወጣ በመሆኑ አዋጁም ይህንን ታሳቢ ባደረገ መልኩ እንዲዘጋጅ ጠይቀዋል።።

መታወቂያው አንድ ሰው የተለያየ ሀሰተኛ መታወቂያ በመጠቀም ለማጭበርበር የሚያደርገውን ጥረት እንደሚያስቀር በማንሳት።

የብሔራዊ መታወቂያ ፕሮጀክት ጽህፈት ቤት ዋና ስራ አስፈጻሚ ዮዳሄ አርዓያስላሴ በበኩላቸው፤ የመታወቂያው የመሰጠት ዓላማ አንድ ሰው አንድ መታወቂያ እንዲኖረው ለማድረግ እንጂ የወሳኝ ኩነት መረጃዎችን ለመተካት አይደለም ብለዋል።

መረጃው ከጣት አሻራ፣ ከዓይን እና ከፊት ገጽታ የሚወሰድ መሆኑን ጠቅሰው፤ አንድን ሰው ከሌላ በመለየት  ወንጀልን ለመከላከል ያግዛል ነው ያሉት።

ይህም በተለያየ ሀሰተኛ ሰነድ በማጭበርበር በአገሪቱ ኢኮኖሚ ላይ ሲደርስ የነበረውን ጉዳት የሚያስቀር መሆኑን ጠቁመዋል።

የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የህግ፣ የፍትህና ዲሞክራሲያዊ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አባል እውነቱ አለነ በበኩላቸው የቀረቡት ሀሳቦች ረቂቅ አዋጁን ለማዳበር ጥሩ ግብዓት መሆናቸውን ጠቁመው በቀጣይ በአዋጁ እንደሚካተቱ ተናግረዋል።

በተያዘው በጀት ዓመት ከ12 ሚሊዮን በላይ ለሚሆኑ ዜጐች ብሔራዊ መታወቂያውን ተደራሽ ለማድረግ እቅድ መያዙም በውይይት ወቅት ተነስቷል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም