በአማራ ክልል ከ131 ቢሊዮን ብር በላይ ካፒታል ላስመዘገቡ ባለሀብቶች የኢንቨስትመንት ፈቃድ ተሰጠ

102

ባህር ዳር (ኢዜአ) ህዳር 5/2015 በአማራ ክልል በ2015 ዓ.ም በመጀመሪያ ሩብ ዓመት 131 ነጥብ 4 ቢሊዮን ብር ካፒታል ላስመዘገቡ ባለሀብቶች በአምራች ኢንዱስትሪ ዘርፍ የኢንቨስትመንት ፈቃድ መሰጠቱን የክልሉ ኢንዱስትሪና ኢንቨስትመንት ቢሮ ገለጸ።

የቢሮው ሃላፊ አቶ እንድሪስ አብዱ በባህር ዳር ከተማ በ1 ነጥብ 5 ቢሊዮን በር የተገነባው ዩኒሰን ዘይት ማምረቻ ፋብሪካ ትናንት ሲመረቅ እንደገለጹት፣ በሩብ ዓመቱ ፈቃድ የተሰጠው ለ1 ሺህ 180 ባለሀብቶች ነው።

በዋናነት በማኑፋክቸሪን፣ በግብርና እና በቱሪዝም ዘርፍ ለመሰማራት ፈቃድ የወሰዱት ባለሀብቶች ቁጥር ካለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር በ870 ብልጫ እንዳለው አስረድተዋል።

የክልሉን ኢንቨስትመንት በዘላቂነት ለማሳደግ ከሀይል አቅርቦት፣ ከአገልግሎት አሰጣጥ እና ከአሰራር ጋር ሲስተዋሉ የነበሩ ችግሮች እየተፈቱ በመምጣታቸው በክልሉ መዋዕለ ንዋያቸውን የሚያፈሱ የባለሀብቶች ቁጥር እንዲያድግ አስተዋጽኦ ማድረጉን ተናግረዋል።

ባለሀብቶቹ ግንባታቸውን አጠናቀው በሙሉ አቅም ወደ ማምረት ሲገቡ ለ263 ሺህ 737 ዜጎች ቋሚ የሥራ ዕድል እንደሚፈጥሩም አስታውቀዋል።

በክልሉ በአሁኑ ወቅት 3ሺህ 443 አምራች ኢንዱስትሪዎች መኖራቸውን ገልጸው፣ ከእነዚህ ወስጥ 755ቱ የግብርና ምርቶችን በግብአትነት የሚጠቀሙ ናቸው ብለዋል።

የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ዶክተር ይልቃል ከፋለ እንዳሉት ባለሃብቶች መሬት ወስደው ለረዥም ጊዜ ሳያለሙ ማስቀመጥ ከራሳቸው ባለፈ የአካባቢውና የክልሉ የልማት እንቅስቃሴን የሚጎዳ ነው።

የክልሉ መንግስት ለአልሚ ባለሀብቶች ተገቢውን ድጋፍ እንደሚያደርግ ገልጸው፣ መሬት ተረክበው ሳያለሙ አጥረው ለረዥም ጊዜ ያስቀመጡ ባለሀብቶች ላይ ህጋዊ የማስተካከያ እርምጃ እንደሚወሰድም ገልጸዋል።

ባለሀብቱ መሬቱን ከተረከበ በኋላ በተቻለ ፍጥነት ሰርቶ ለታለመለት ዓላማ በማዋል ለክልሉ የኢኮኖሚ እድገት የድርሻውን ሊወጣ እንደሚገባ አስገንዝበዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም