የታላቁ የሕዳሴ ግድብ ዋንጫ በስምንት ቀናት የአምቦ ከተማ ቆይታው 10 ሚሊዬን ብር ተሰበሰበ

123

አምቦ (ኢዜአ) ህዳር 5 ቀን 2015 የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ዋንጫ በስምንት ቀናት የአምቦ ከተማ ቆይታው 10 ሚሊዬን ብር  በቦንድ ሽያጭ መሰብሰቡን የከተማው ኮሙዩኒኬሽን ጽህፈት ቤት ገለጸ።

የአምቦ ከተማ አስተዳደር ለታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ የሚውል ገቢ ለማሰባሰብ ከጉደር ከተማ የሕዳሴ ዋንጫ መረከቡን ጽህፈት ቤቱ አስታውሷል።

የጽህፈት ቤቱ ኃላፊ አቶ መብራቱ ታደሰ ለተሰበሰበው ገንዘብ የከተማዋ ነዋሪዎች፣ ባለሀብቶች፣ ነጋዴዎችና የመንግስት ሰራተኞች ትልቅ ተሳትፎ ማድረጋቸውን ገልጸዋል።

ከተማ አስተዳደሩ የግድቡ ግንባታ ተጠናቆ ለፍፃሜ እስከሚደርስ ድረስ በቦንድ ግዥና ስጦታ መልክ የሚያደርገውን ድጋፍ የሚያጠናክር መሆኑንም አንስተዋል።

ኢዜአ ያነጋገራቸው የአምቦ ከተማ ነዋሪ አቶ ለማ ኡርጌሳ የ10 ሺህ ብር ቦንድ መግዛታቸውንና በቀጣይም የግድቡ ግንባታ እስኪጠናቀቅ ድጋፋቸውን እንደሚቀጥሉ ተናግረዋል፡፡

''ግድቡ የማንነታችንና የህልውናችን መሠረት በመሆኑ ድጋፌን አጠናክራለሁ'' ያሉት ደግሞ ወይዘሮ ሙሉነሽ አበራ ናቸው፡፡

ዋንጫው በከተማ አስተዳደሩ የነበረውን ቆይታ አጠናቆ ወደ ምስራቅ ጉጂ ዞን መሸኘቱንም ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም