ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አህመድ በነገው እለት ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ማብራሪያ ይሰጣሉ - ኢዜአ አማርኛ
ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አህመድ በነገው እለት ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ማብራሪያ ይሰጣሉ
195
አዲስ አበባ (ኢዜአ) ህዳር 5/2015 ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አህመድ በነገው እለት ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ጥያቄ ማብራሪያ እንደሚሰጡ ተገለጸ፡፡
የኢትዮጵያ ፌደራላዊ ዲሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ 6ኛው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በ2ኛ ዓመት የስራ ዘመኑ ነገ ህዳር 06 ቀን 2015 ዓ.ም ከጠዋቱ 2፡30 ጀምሮ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አህመድ በተገኙበት 4ኛ መደበኛ ስብሰባውን እንደሚያካሂድ የምክር ቤቱ የኮሙኒኬሽን ዳይሬክቶሬት ለኢዜአ ገልጿል፡፡
በመደበኛ ስብሰባው የኢፌዴሪ ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ መስከረም 30 ቀን 2015 ዓ.ም ለሕዝብ ተወካዮች እና ለፌዴሬሽን ምክር ቤቶች የጋራ ስብሰባ ያደረጉትን የመክፈቻ ንግግር አስመልክቶ ከምክር ቤቱ አባላት በሚቀርቡ ጥያቄዎች ላይ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ምላሽና ማብራሪያ እንደሚሰጡ አመላክቷል።
በዚህም ምክር ቤቱ የመንግስትን አቋም በማዳመጥ የድጋፍ ሞሽኑን ያፀድቃል ተብሎ እንደሚጠበቅ ገልጿል፡፡
በዕለቱ በአዲስ አበባ የሚገኙ የተለያዩ አገራት አምባሳደሮችና የዓለም አቀፍ ተቋማት ተጠሪዎች፣ የሐይማኖት አባቶች እና ሌሎች ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች እንደሚገኙ አስታውቋል።