የድሬዳዋ አስተዳደር ምክር ቤት አዳዲስ የካቢኔ አባላትን ሾመ

57
ድሬደዋ መስከረም 16/2011 የድሬዳዋ አስተዳደር ምክር ቤት ዛሬ ባካሄደው 3ተኛ አስቸኳይ ጉባኤ ምክትል አፈ-ጉባኤን ጨምሮ የተጓደሉ የስድስት ካቢኔ አባላትን ሹመት አጸደቀ። ጉባኤው የአንድ የምክር ቤት አባል ያለመከሰስ መብትን በማንሳት ተጠናቋል። የተጓደሉትን የካቢኔ አባላት በአዳዲስ መተካቱ በየደረጃው የሚገኘው ህብረተሰብ የሚፈለገውን ልማትና የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎች ለማሳካት እንደሚያስችል ከንቲባ ኢብራሂም ዑስማን ተናግረዋል፡፡ በጉባኤው መክፈቻ ላይ የምክር ቤቱ አፈ-ጉባኤ አብዱሰላም መሐመድ እንደተናገሩት ምክር ቤቱ 3ተኛውን አስቸኳይ ጉባኤ ያካያሄደው በትምህርትና በሌላ ምክንያት የተጓደሉትን ስድስት የካቢኔ አባላትና ምክትል አፈ-ጉባኤን ለማሟላት ነው። "ይህም በልማት፣ በመልካም አስተዳደር፣ በፍትህ ጉዳዮች ላይ ዘንድሮ ሊከናወኑ የተያዙ አንኳር ጉዳዮች በተገቢው መንገድ ለማሳካት ያግዛል" ብለዋል፡፡ ጉባኤው የምክር ቤቱ አባልና የፍትህ፣ ፀጥታና የህግ ጉዳዮች ቢሮ ኃላፊ የነበሩትን የአቶ መሀመድ አህመድን ያለመከሰስ መብታቸውን በሙሉ ድምጽ እንዲነሳ ወስኗል፡፡ በጉባኤው ላይ እንደተገለጸው ምክር ቤቱ የግለሰቡን ያለመከሰስ መብታቸው እንዲነሳ የወሰነው የሶማሌና የኦሮሞ ህዝቦች እንዲጋጩ በገጠርና በከተማ ቅስቀሳ አድርገዋል፤ ህገ-ወጥ የጦር መሳሪያ አስታጥቀዋል፣ "ሄጎ" የተባለ የጥፋት ቡድን በማደራጀት ለጥፋት እንዲነሳ ከመቀስቀሳቸው ባለፈ በኤግዚቢትነት የተያዘ የጦር መሳሪያ፤ የሰውና የሰነድ ማስረጃን ፖሊስ ለምክር ቤቱ በማቅረቡ ነው። የምክር ቤቱ የፍትህ፣ ፀጥታና የህግ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴም ጉዳዩን አጣርቶ የግለሰቡ የህግ ከለላ እንዲነሳ መወሰኑን አስታውቋል፡፡ በጉባኤው በእሳቸው ምትክ አቶ ኢብራሂም ዩሱፍን የፍትህ፣ የፀጥታና የህግ ጉዳዮች ቢሮ ኃላፊ  ሆነው ተሹመዋል። ከዚህ በተጨማሪ ምክር ቤቱ በትምህርት ሳቢያ ከሥራ ገበታቸው የተለዩ 4 የካቢኔ አባላትና የምክር ቤቱ ምክትል አፈ-ጉባኤ ምትክ አዳዲስ አመራሮች ሾሟል፡፡ በእዚህ መሰረት አቶ ኡስማን አህመድን የምክር ቤቱ ምክትል አፈ-ጉባኤ፣  አቶ እዝቅያስ ታፈሰን የመንግስት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ ኃላፊ ፣ አቶ ሙሳ ጠሃን የግብርና ውሃ ማዕድንና ኢነርጂ ቢሮ ኃላፊ ሆነው ተሹመዋል። በተጨማሪም ምክር ቤቱ አቶ አቡበከር አብዶሽን የፐብሊክ ሰርቪስና የሰው ሃብት ልማት ቢሮ ኃላፊ፣ ኢንጂነር ጀማል ኢብራሂምን የኮንስትራክሽን፣ የቤቶች ልማትና አስተዳደር ቢሮ ኃላፊ እንዲሁም ዶክተር ፉአድ ከድር የጤና ጥበቃ ቢሮ ኃላፊ በማድረግ ሾሟል፡፡ የድሬዳዋ ምክር ቤት 3ተኛው አስቸኳይ ጉባኤው ከካቢኔ ሹመት በተጨማሪ አቶ ሱልጣን አልይን የዋና ኦዲተር ጽህፈት ቤት ዋና ኦዲተር አድርጎ ሹመታቸውን በሙሉ ድምጽ አጽድቋል፡፡ ዕጩ የካቢኔ አባላት እንዲሾሙ ለምክር ቤቱ ያቀረቡት የአስተዳደሩ ከንቲባ ኢብራሂም ዑማስን እንዳሉት በተጓደሉት ቦታ በአዲስ  የተተኩት የካቢኔ አባላት የተፈጠረን የአመራር ክፍተት መድፈን የሚያስችሉ ናቸው። "በተጨማሪ በዘንድሮ በጀት ዓመት የህብረተሰቡን አንገብጋቢ የልማትና የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎች በላቀ ደረጃ ለመፈፀም የሚያግዙ ይሆናሉ" ብለዋል፡፡ አዲሶቹ አመራሮችም  በአስተዳደሩና ህዝቡ የጣለባቸውን ታላቅ ኃላፊነት ለመወጣት ሌት ተቀን በቁርጠኝነት እንደሚሰሩ ቃል ገብተዋል፡፡
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም