ኢኮኖሚውን ለሚደግፉ ባለሃብቶች መንግስት ተገቢውን እገዛ ያደርጋል-ርዕሰ መስተዳድር ዶክተር ይልቃል ከፋለ

159

ባህር ዳር ህዳር 4/2015 (ኢዜአ) በተለያዩ የኢንቨስትመንት መስኮች ተሰማርተው የክልሉን ኢኮኖሚ ለሚደግፉ ባለሃብቶች መንግስት ተገቢውን እገዛ ያደርጋል ሲሉ የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ዶክተር ይልቃል ከፋለ አስታወቁ።

በባህር ዳር ከተማ በ1 ነጥን 5 ቢሊዮን ብር ወጭ የተገነባ የምግብ ዘይት ፋብሪካ ዛሬ ተመርቋል።

ርዕሰ መስተዳደሩ በወቅቱ እንዳሉት  ''ዩኒሰን'' የምግብ ዘይት ማምረቻ ፋብሪካ እንደ ሀገር በተለይም ክልሉ በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ ባለበት ወቅት በአጭር ጊዜ ተጀምሮ የተጠናቀቀና በአርያነት ሊወሰድ የሚችል ነው።

ፋብሪካው በአጭር ግዜ መጠናቀቁ  መሬትን ወስደው ለበርካታ ጊዜ አጥረው ለሚያስቀምጡ ባለሃብቶች ትልቅ ትምህርት የሚወሰድበት መሆኑን ገልጸዋል።

በክልሉ በተለያየ የኢንቨስትመንት መስኮች የተሰማሩ ባለሃብቶች ለሚያነሷቸው ጥያቄዎች አቅም በፈቀደ መጠን አስፈላጊው ድጋፍ እንደሚያደርግ አመልክተዋል።

በተለይም የህብረተሰቡን ችግሮች በማቃለል፣ የስራ እድል  በመፍጠርና የቴክኖሎጂ ሽግግር በማድረግ የክልሉን ኢኮኖሚ በሚደግፉ የኢንቨስትመንት ዘርፎች ለሚሰማሩ ባለሀብቶች ተገቢው ድጋፍ እንደሚደረግ አስታውቀዋል።

ርእሰ መስተዳድሩ አክለውም የህዝብና የመንግስት መሬት በኢንቨስትመንት ስም ወስደው ለረዥም ጊዜ አጥረው በሚቀመጡ ባለሃብቶች ላይ ህጋዊ እርምጃ እንደሚወሰድም አስገንዝበዋል።

"የ”ዩኒሰን” ዘይት ፋብሪካ ግንባታ ሁለት ዓመት ባልሞላ ጊዜ ውሰጥ ተጠናቆ ወደ ምርት መሸጋገሩ ለከተማው የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ የላቀ ሚና አለው" ያሉት ደግሞ  የባህር ዳር ከተማ  አስተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ዶክተር ድረስ ሳህሉ ናቸው።

“ፋብሪካው ለከተማ አስተዳደራችን ሞዴል ፋብሪካ  ነው” ያሉት ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ናችው ለባለሀብቶች በችግር ውስጥም ተሁኖ የተሻለ ስራ መስራት እንደሚቻል ያሳየ እንደሆነም ተናግረዋል።

የዩኒሴን ኮርፖሬት አባል አቶ ይልቃል ካሴ በበኩላቸው "ፋብሪካው የኢንቨስትመንት ስራውን ሲጀምር ታሳቢ ያደረገው የአገሪቱን የዘይት ፍላጎትና አቅርቦት ለማጣጣም በሚደረገው ጥረት የራሱን ድርሻ ለመወጣት ነው" ብለዋል።

"የምግብ ዘይት ፋብሪካው እንደ ሀገር የምግብ ዘይት አቅርቦት ችግርን ለመቅረፍ በሚደረገው ጥረት ክፍተት ለመሙላት ከማገዝ ባለፈ በአገር ውስጥ ባለሃብቶች ብቻ የተገጣጠመ በመሆኑ በራስ አቅም መስራት እንደሚቻል ጭምር ያሳየ ፋብሪካ ነው" ሲሉም አክለዋል።

አቶ ይልቃል  አክለው ፋብሪው ከ1 ነጥብ 5 ቢሊዮን ብር በላይ ወጭ የተደረገበትና በቀን ከ30 ሺህ ሊትር በላይ የምግብ ዘይት የማምረት አቅም እንዳለው አመልክተዋል።

በአሁኑ ወቅት ለ180 ሰዎች ቋሚና ጊዜያዊ የስራ እድል መፍጠሩን ጠቅሰው፤ ከተማ አስተዳደሩ ለፋብሪካው ግንባታ ቦታ በመስጠትና በሌሎችም ላደረጋቸው መሰል ድጋፎች አመስግነዋል።

በምረቃ-ስነ ስርዓቱ ላይ የክልሉ ከፍተኛ የስራ ሃላፊዎች፣ ባለሃብቶችና የአካባቢው ማህበረሰብ ተገኝተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም