በጦርነቱ ጉዳት የደረሰባቸው የህብረተሰብ ክፍሎችንና ተቋማትን ለማቋቋም አስፈላጊውን ድጋፍ ይደረጋል -ርእሰ መስተዳድር ኦርዲን በድሪ

109

ሀረር ህዳር 4/2015 9ኢዜአ) በሰሜኑ የሃገራችን ክፍል በጦርነት ጉዳት የደረሰባቸው የህብረተሰብ ክፍሎችና ተቋማትን ለማቋቋም የክልሉ መንግስት አስፈላጊውን ድጋፍ ያደርጋል ሲሉ የሀረሪ ክልል ርእሰ መስተዳድር አቶ ኦርዲን በድሪ አስታወቁ።

ርዕሰ መስተዳድር አቶ ኦርዲን በድሪ በወቅታዊ ሀገራዊ ጉዳይ ላይ ዛሬ መግለጫ ሰጥተዋል ።

ርእሰ መስተዳድሩ በመግለጫቸው እንዳስታወቁት የክልሉ መንግስትና ህዝብ  የሰላም ስምምነቱ በአግባቡ ተፈፃሚ እንዲሆን በሙሉ ልብ ይደግፋሉ።

በጦርነቱ ጉዳት የደረሰባቸው የህብረተሰብ ክፍሎችና ተቋማትን መልሶ ለማቋቋም በሚደረገው ጥረት አስፈላጊው ድጋፍ እንደሚደረግ አስታውቀዋል።

ከሰላም የሚበልጥ ጉዳይ ባለመኖሩ ዘላቂ ሰላምን የሚያረጋግጥ ስምምነት ላይ መደረሱ ትልቅ ድል መሆኑን ተናግረዋል።

የሰላም ስምምነቱ በሀገሪቱ ሰላምን ለማስፈንና ልማትን ለማረጋገጥ መሰረት የሚጥል እና መንግስትና ህዝቡ ፊታቸውን ሙሉ በሙሉ ወደ ልማት እንዲያዞሩ እድል የሚፈጥር መሆኑንም አክለዋል ።

ሰላምን እውን ማድረግ ከመነሻውም  የመንግስት ፍላጎት እንደነበር አስታውሰው በስምምነቱ የተደረሰባቸው ጉዳዮች ተግባራዊ እንዲሆኑ ሁሉም ዜጋ የበኩሉን አስተዋጾ በማበርከት አገራዊ ግዴታውን እንዲወጣ ጥሪ አቅርበዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም