ህብረተሰቡ ጤናማ የአኗኗር ባህልን በማጎልበት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ የመጣውን የስኳር ህመም ሊከላከል ይገባል

105

ህዳር 4 ቀን 2015(ኢዜአ) ህብረተሰቡ ጤናማ የአኗኗር ባህልን በማጎልበት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ የመጣውን የስኳር ህመም መከላከል እንዳለበት የኢትዮጵያ ስኳር ህመም ማህበር ጥሪ አቀረበ፡፡

የስኳር ህመም የሚከሰተው ሰውነታችን  የሚያስፈልገውን የስኳር መጠን በትክክል መጠቀም ሳይችል ሲቀር መሆኑን የህክምና ባለሙያዎች ይገልጻሉ።

በዓለም ዓቀፍ ደረጃ 516 ሚሊዮን ሰዎች ከስኳር ህመም ጋር አብረው እንደሚኖሩ መረጃዎች የሚያመላክቱ ሲሆን፤ከእነዚህም ውስጥ አብዛኛዎቹ ሁለተኛው ዓይነት የስኳር ህመም ያለባቸው ናቸው፡፡

ከዓይነት አንድ የስኳር ህመም ጋር የሚኖሩ ህጻናትና ወጣቶች ቁጥርም በዓለም ላይ በሦስት በመቶ እየጨመረ መሆኑን ነው መረጃዎች የሚጠቁሙት፡፡

በኢትዮጵያም የስኳር ህሙማን ቁጥር ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ መጥቷል፡፡

የኢትዮጵያ ስኳር ህመም ማህበር ፕሬዝዳንት ዶክተር ጌታሁን ታረቀኝ  እንደሚሉት፤ በኢትዮጵያ ከ 3 ነጥብ 2 በመቶ በላይ የሚሆኑ ዜጎች ከስኳር ህመም ጋር አብረው ይኖራሉ፡፡

9 ነጥብ 2 በመቶ የሚሆኑት ደግሞ በቅድመ ስኳር ሁኔታ ውስጥ እንደሚኖሩ ጠቅሰው፤ "ቅድመ ስኳር" ማለት የስኳር ህመም ደረጃን ያላሟላና ወደ ስኳር ህመም የመሸጋገር አቅሙ ከፍተኛ መሆኑን አብራርተዋል፡፡

ጤናማ የአኗኗር ዘይቤን አለመከተል ደግሞ ለስኳር ህመም መጨመር ከፍተኛ ሚና እንዳለው ነው የተናገሩት፡፡

በተለይ ስፖርታዊ እንቅስቃሴን አዘውትሮ አለመተግበር፣ የታሸጉና ጣፋጭ ምግቦችን ማዘውተር፣ የአልኮል መጠጥ፣ሲጋራና ሌሎች ሱሶች የህመሙ ስርጭት እንዲጨምር ማድረጋቸውንም ገልጸዋል፡፡

በመሆኑም ህብረተሰቡ ጤናማ የአኗኗር ዜይቤን በመከተል የስኳር ህመምን መከላከል እንዳለብት መክረዋል፡፡

ስፖርታዊ እንቅስቃሴን ጨምሮ ሌሎች ጤናማ የአኗኗር ሁኔታን በመተግበር ሁለተኛው ዓይነት የስኳር ህመምን እስከ 80 በመቶ መከላከል እንደሚቻልም ተናግረዋል፡፡

በተጨማሪ ህብረተሰቡ የስኳር ህመም ምርመራ የማድረግ ባህሉን ሊያጎለብት እንደሚገባም እንዲሁ፡፡

ከዚህ አኳያ ማህበሩ ከጤና ሚኒስቴርና ሌሎች አጋር አካላት ጋር በመሆን የግንዛቤ ማስጨበጥ ስራ፣ የመድሐኒት አቅርቦትና የህክምና ተደራሽነትን ማስፋትና ሌሎች ተግባራትን እያከናወነ መሆኑን  አብራርተዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም