የኢትዮጵያን ከፍታ ለማረጋገጥ ችግሮችን ተቋቁሞ በቅንጅት መስራት ይገባል

117

ደሴ (ኢዜአ) ህዳር 4/2015  የኢትዮጵያን ከፍታ ለማረጋገጥ ችግሮችን ተቋቁሞ በቅንጅት መስራት እንደሚገባ  የመከላከያ ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር አህመዲን መሐመድ አሳሰቡ፡፡

ወሎ ዩኒቨርሲቲ ለ14ኛ ጊዜ በተለያየ መርሃ ግብር በመጀመሪያና ሁለተኛ ዲግሪ ያሰለጠናቸውን 6 ሺህ 308 ተማሪዎች አስመርቋል።

ሚኒስትር ዴኤታው ዶክተር አህመዲን በዚሁ ጊዜ እንዳሉት ኢትዮጵያ በተለያየ ጊዜ ፈተና ቢገጥማትም በኢትዮጵያውያን የተባበረ ጥረት ስትሻገር ኑራለች።

የሚገጥሙንን ሰው ሰራሽና የተፈጥሮ ችግሮችን ተቋቁመን የኢትዮጵያን ከፍታ ለማረጋገጥ በቅንጅት መስራት ይገባናል ያሉት ዶክተር አህመዲን፤ ባለፉት ሁለትና ሶስት ዓመታት የነበሩብንን ፈታኝ ጊዜያት አልፈን የአገር ብልጽግና እውን ለማድረግ እየሰራን ነው ብለዋል።

"እነዚህ ያሳለፍናቸው ጊዜያት ያስተማሩን የውስጥ ችግሮቻችንን በራሳችን የመፍታት አቅማችንን እያጎለበትን መሆናችን ነው" ያሉት ሚኒስትር ዴኤታው፤ ለዚህ ሁሉም ዜጋ ሊረባረብ ይገባል ነው ያሉት።

በእውቀት ታግዞ በመነጋገር፣ በመወያየትና በሃሳብ የበላይነት ችግሮችን የመፍታት ባህላችን የበለጠ ጎልብቶ እንዲቀጥል ሁሉም ኢትዮጵያዊ በተለይም የተመራቂዎቹ ሚና ከፍተኛ መሆኑን በማውሳት።

ህብረተሰቡ የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት ለማስጠበቅ ድንቅ የአብሮነት ባህልና እሴቱን ጠብቆ በአንድነት መስራትና የኢትዮጵያን ትንሳኤ ማብሰር አለበት ሲሉም አሳስበዋል።

የወሎ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ዶክተር መንገሻ አየነ በበኩላቸው ዩኒቨርስቲው እንደ ሌሎቹ አቻ ዩኒቨርሲቲዎች ለኢትዮጵያ አንድነትና ዘላቂ ሰላም መጎልበት በትኩረት ይሰራል ብለዋል።

በተለይም ሀገር በቀል እውቀቶችን በጥናትና ምርምር በማጎልበት ከሀገር ሽማግሌዎች፣ የሐይማኖት አባቶችና ባለድርሻ አካላት ጋር በቅንጅት እየሰራ መሆኑን ተናግረዋል።

ምሩቃን ተማሪዎችም በዩኒቨርስቲው ቆይታቸው ያገኙትን እውቀት ተጠቅመው ለኢትዮጵያ አንድነትና ሰላም በመስራት የድርሻቸውን እንዲወጡ አሳስበዋል።

ዩኒቨርሲቲው ለ14ኛ ጊዜ ካስመረቃቸው 6 ሺህ 308 ተመራቂዎች መካከልም 468ቱ በሁለተኛ ዲግሪ የተመረቁ መሆናቸው ታውቋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም