በምዕራብ ጎንደር ዞን ገንዳ ውኃ ከተማ የደረሰ ቃጠሎ ከፍተኛ የንብረት ውድመት አስከተለ

105
መተማ ግንቦት 11/2010 በምዕራብ ጎንደር ዞን ገንዳ ውኃ ከተማ ካልሚ ትሬዲንግ ሃላፊነቱ የተወሰነ የግድል ድርጅት መጋዝን ላይ የተነሳ የእሳት አደጋ ከፍተኛ የንብረት ውድመት ማድረሱን የገንዳ ውሃ ከተማ  ፖሊስ ጽህፈት ቤት አስታወቀ። የፅህፈት ቤቱ ሃላፊ ኢንስፔክተር ሃይማኖት ከፋለ ለኢዜአ እንደገለፁት ትላንት ከእኩለ ሌሊት በኋላ ባልታወቀ ምክንያት የተነሳው ቃጠሎ በመጋዘኑ ውስጥ የተከማቸውን የጥጥ ምርት አውድሟል። አደጋውን ለመከላከል የአካባቢው ማህበረሰብ ከፀጥታ መዋቅሩ ጋር በመቀናጀት ርብርብ እያደረገ ቢሆንም ጥጥ በተፈጥሮው ካለው የመንደድ ባህሪ ጋር በተያያዘ በፍጥነት መቆጣጠር እንዳልተቻለ ገልጸዋል። የእሳት አደጋውን በሰው ሃይል መቆጣጠርም ባለመቻሉም ከጎንደር ሁለት ከሱዳን ገዳሪፍ ደግሞ አንድ የእሳ አደጋ መኪና በማስመጣት ለመቆጣጠር ጥረት ቢደረግም እስከ አሁን ድረስ እሳቱ ሙሉ በሙሉ አልጠፋም። አደጋው ያደረሰው የጉዳት መጠንና የችግሩ መንስኤ እየተጣራ መሆኑንም ኢንስፔክተር ሃይማኖት ገልጸው እንዲህ ዓይነት ቃጠሎ በሌሎች የኢንዱስትሪ መንደሮች ሊከሰት ስለሚችል አስፈላጊው ጥንቃቄ መደረግ እንዳለበት አሳስበዋል። የድርጅቱ ስራ አስኪያጅ አቶ ሰሎሞን ገብረስላሴ በበኩላቸው በድርጅቱ ሶስት መጋዝኖች ውስጥ የሚገኝና እስከ 40 ሚሊዮን ብር የሚገመት ከ12 ሺህ ኩንታል በላይ ጥጥ ሙሉ በሙሉ መውደሙን ተናግረዋል። በሌሎች መጋዝኖች ተከማችተው የነበሩ የሰሊጥና ቦለቄ ምርቶችን በወቅቱ በተደረገ ርብርብ ማትረፍና ወደ ሌላ ቦታ እንዲጫኑ መደረጉን ተናግረዋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም