የባንክ ዘርፉን ለውጭ ባለሀብቶች ክፍት የማድረግ ሂደት ውስን ቁጥር ባላቸው የውጭ ባንኮች ብቻ ይጀመራል - ብሔራዊ ባንክ

130

አዲስ አበባ (ኢዜአ) ህዳር 3 ቀን 2015 በኢትዮጵያ የባንክ ዘርፉን ለውጭ ባለሀብቶች ክፍት የማድረግ ሂደት ውስን ቁጥር ባላቸው የውጭ ባንኮች ብቻ የሚጀመር መሆኑን የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ አስታወቀ።

በኢትዮጵያ ለዓመታት ለውጭ ባለሀብቶች ዝግ ሆኖ የቆየው የባንክ ዘርፍ በቅርቡ ክፍት እንዲሆን መወሰኑ ይታወቃል።

የሚኒስትሮች ምክር ቤት ነሐሴ 28 ቀን 2014 ዓ.ም ባካሄደው መደበኛ ስብሰባ የባንክ ዘርፉን ለውጭ ባለሀብቶች ክፍት የሚያደርገውን አሰራር እውን አድርጓል።

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ የፋይናንስ ተቋማት ሱፐርቪዥን ምክትል ገዥ አቶ ሰለሞን ደስታ ለኢዜአ እንዳሉት፤ የውጭ ባንኮች የካበተ ልምድ ይዘው ስለሚመጡ የሀገር ውስጥ ባንኮችን ለማነቃቃት ትልቅ እድል ነው።

የውጭ ባንኮች ይዘውት የሚመጡት ካፒታል በኢትዮጵያ ያለውን የውጭ ምንዛሬ እጥረት በማቃለል ለተጨማሪ ኢንቨስትመንት ምቹ ሁኔታ ይፈጥራል ብለዋል።

መንግስት በኢትዮጵያ በባንክ ዘርፍ ለመሳተፍ የሚመጡ የውጭ ባንኮችን በሙሉ ተቀብሎ ፈቃድ እንደማይሰጥ የገለጹት አቶ ሰለሞን፤ ለመነሻነት ውስን የውጭ ባንኮችን ብቻ እንደሚያስተናግድ ተናግረዋል።

ለዚህም አራት ቅድመ ሁኔታዎች ተዘጋጅተዋል ብለዋል።

ፈቃድ ማግኘት የሚችሉት በኢትዮጵያ ንዑስ ባንክና ቅርንጫፍ ለማቋቋም የሚጠይቁና ከሀገር ውስጥ ባንኮች እስከ 40 በመቶ አክሲዮን የሚገዙ የውጭ ባንኮች መሆናቸውን አብራርተዋል።

ከአገልግሎት አንፃርም በተለይ ለግብርና፣ ለቤትና ሌሎች መሰረተ ልማት ግንባታ እንዲሁም ለገጠር አካባቢዎች የተለያዩ አገልግሎት ለመስጠት አልመው የሚመጡ ባንኮች የሚኖራቸው ፋይዳ ጉልህ እንደሚሆን ተናግረዋል።

አራቱን ቅድመ ሁኔታዎች ያሟሉ የውጭ ባንኮች ኢንቨስት ለማድረግ ከገቡ ለኢትዮጵያ የፋይናንስ ዘርፍ ትልቅ አበርክቶ ይኖራቸዋል ብለዋል።

የውጭ ባንኮች መልካም እድል ይዘው እንደሚመጡት ሁሉ ስጋቶች እንደሚኖሩም ጠቁመዋል።

ስጋቶችን ለመቀነስም በዘርፉ ያለው ልምድ እየዳበረ እስከሚሄድ ድረስ ወደ አገር ውስጥ የሚገቡ የውጭ ባንኮችን ቁጥር በመገደብና አስፈላጊውን ክትትል በማድረግ በትኩረት ይሰራል ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም