የተመድ ዋና ጸሀፊ አንቶኒዮ ጉተሬስ የኢትዮጵያን የማሻሻያ ስራዎች አደነቁ

99
አዲስ አበባ መስከረም 16/2011 የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት (ተመድ) ዋና ጸሀፊ አንቶኒዮ ጉተሬስ  ኢትዮጵያ የጀመረቻቸውን የለውጥ ስራዎች ማድነቃቸውን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ገለጸ። የሚኒስቴሩ ቃል አቀባይ ጽህፈት ቤት ለኢዜአ በላከው መግለጫ እንዳመለከተው፤ ዋና ጸሀፊ አንቶኒዮ ጉቴሬዝ በኢትዮጵያ እየተካሄዱ የሚገኙ የማሻሻያ ስራዎችን በተለይም የፍትህ ስርዓት ማሻሻያዎችን አድንቀዋል፡፡ ዋና ጸሀፊው በተመድ ጠቅላላ ጉባኤ  ትናንት በተካሄደ ውይይት ላይ ባደረጉት ንግግር በኢትዮጵያ የፖለቲካ ምህዳሩን ለማስፋት የተጀመረው ሂደት እንዲሁም በተለያዩ ምክንያቶች የታሰሩ ዜጎች መፈታታቸው ትክክለኛ ውሳኔ መሆኑን ተናግረዋል። ተመድ በኢትዮጵያ እየተከናወኑ ያሉ የፍትህ ስርዓት ማሻሻያዎችን ለመደገፍ ዝግጁ እንደሆነም ጠቁመዋል። በተመድ 73ኛ ጠቅላላ ጉባዔ ላይ ለመሳተፍ በኒውዮርክ የሚገኘው የኢትዮጵያ ልዑካን ቡድን አባል የሆኑት ጠቅላይ ዐቃቤ ህግ አቶ ብርሃኑ ፀጋዬ በተመድ በኩል የቀረበው ሃሳብ የሚያበረታታ እንደሆነ መናገራቸውን መግለጫው አመልክቷል። በተያያዘ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዶክተር ወርቅነህ ገበየው ተመድ ብቻውን የሰላምና ደህንነት ስጋቶችንና ተግዳሮቶችን መቆጣጠር የማይችል በመሆኑ ለዓለም ሰላም መረጋገጥ የተቀናጀ ጥረት እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል። በሰላም ማስከበር ጉዳይ በተዘጋጀ የመሪዎች መድረክ ላይ ሚኒስትሩ እንደተናገሩት፤ ሰላምና ደህንነት የማረጋገጡ ጉዳይ በአካባቢያዊና በባለብዙ መድረኮች የሚከናወን በመሆኑ በዚህ ደረጃ ማሻሻያ ማድረግ ያስፈልጋል፡፡ በዓለም አቀፍ የሰላም ማስከበር እንቅስቃሴ ውስጥ ኢትዮጵያ ግንባር ቀደም ሚና እየተጫወተች እንደምትገኝ የጠቀሱት ዶክተር ወርቅነህ አገሪቱ በአለም ላይ ሰላምና መረጋጋት እንዲሰፍን የበኩሏን ለመወጣት የፀና አቋም እንዳላት ገልጸዋል፡፡ ኢትዮጵያ የተመድ የሰላም ማስከበር ተልዕኮዎችንና ጥረቶችን ለማሻሻል የሚደረገውን እንቅስቃሴ እንደምትደግፍም መናገራቸውን የሚኒስቴሩ ቃል አቀባይ ጽህፈት ቤት ለኢዜአ የላከው መግለጫ ያመለክታል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም