በተፎካካሪ ፖለቲካ ፓርቲዎች ውስጥ የነበሩ ታጣቂዎች በአንድ ወር ውስጥ ወደ ህብረተሰቡ ይቀላቀላሉ

391

አዲስ አበባ መስከረም 16/2011 በትጥቅ ትግል ተሰማርተው በቆዩ ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች ውስጥ ለነበሩ ታጣቂዎች የተለያዩ የስራ እድሎች በመስጠት ወደ ህብረተሰቡ እንዲቀላቀሉ ለማድረግ የሚያስችሉ ተግባራት እየተከናወኑ መሆኑን የመልሶ ማቋቋም ፕሮጀክት ጽህፈት ቤት አስታወቀ።

በቅርቡ መንግስት በውጪ የሚኖሩ ተፎካካሪ ፓርቲዎች ወደ አገር ውስጥ ተመልሰው በሰላማዊ መንገድ ትግል እንዲያደርጉ ጥሪ አድርጓል።

በኢትዮጵያ የዴሞክራሲ ምህዳሩን ለማስፋትና የሀሳብ ልዕልና አሸናፊ እንዲሆን ለማድረግ የታለመ የሰላም ጥሪ መሆኑን ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ በተደጋጋሚ ገልጸዋል።

በዚሁ መሰረት በውጪ አገሮች የቆዩም ሆኑ የትጥቅ ትግል በማካሄድ ላይ የነበሩ የፖለቲካ ፓርቲዎች አመራር አባላት ወደ አገር ቤት ተመልሰዋል።

በአሁኑ ወቅት በኢትዮጵያ የተጀመረውን የለውጥና የሰላም ጉዞ ከዳር ለማድረስ እንዲቻል በትጥቅ ትግል የተሳተፉ ታጣቂዎች ወደ ሰላማዊ ኑሮ እንዲመለሱ በጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት ስር የመልሶ ማቋቋም ፕሮጀክት ጽህፈት ቤት ተቋቁሟል።

ጽህፈት ቤቱም የተጀመረውን የሰላም ጉዞ እውን ለማድረግ የፖለቲካ ፓርቲዎቹን ታጣቂዎች በማሰልጠንና ድጋፍ በማድረግ ወደ መደበኛ ኑሮ ለማሸጋገር እንዲቻል የተለያዩ ተግባራት እያከናወነ ነው።

የፕሮጀክት ጽህፈት ቤቱ ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ ተስፋዬ ይገዙ ለኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት እንደገለጹት፤ መንግስት የተፎካካሪ ፓርቲዎቹ የቀድሞ ታጣቂዎችን ወደ ተረጋጋና ሰላማዊ ህይወት ለመመለስ ትኩረት ሰጥቷል።

በመንግስት የተደረገውን የሰላም ጥሪ ከተቀበሉትና ወደ አገራቸው ከተመለሱት መካከል የኦሮሞ ነጻነት ግንባር፣ አርበኞች ግንቦት ሰባት፣ የአማራ ዴሞክራሲያዊ ሃይሎች ንቅናቄና የትግራይ ህዝቦች ዴሞክራሲ ንቅናቄ ቀዳሚውን የሚይዙ ናቸው።

አቶ ተስፋዬ እንደሚናገሩት፤ መንግስት የሚያካሂደው የመልሶ ማቋቋም ተግባር የሰላም ግንባታው አንድ አካል ነው።

ለዚህ ቀዳሚ ተግባር አድርጎ ከወሰዳቸው መካከል ታጣቂዎቹን ከጎረቤት አገሮች ወደ አገር ውስጥ ማስገባት አንዱ መሆኑን አመልክተው፤ በእስካሁኑ ሂደት የቀድሞ ታጣቂዎች የሆኑ በባህርዳርና ሁሩታ ካምፖች መግባታቸውን ነው የተናገሩት።

 ለታጣቂዎቹ የሚሰጠው ስልጠና ከትግልና ጦር ሜዳ ኑሮ ወደ ሰላማዊና መደበኛ ህይወት የሚያሸጋግራቸው መሆኑን ጠቁመው፤ ይህም ኑሯቸውን ለመምራትና የህይወት ክህሎት ለመቀየር የሚያስችል እንደሚሆን ነው አቶ ተስፋዬ ያብራሩት።

የቀድሞ ታጣቂዎች የራሳቸውን ህይወት መምራት እንዲችሉ ለማድረግ እየተጣረ መሆኑን አመልክተው፤ “በገጠርና በከተማ የስራ እድል ፈጠራ ፓኬጆች ውስጥ ይካተታሉ” ብለዋል።

የቀድሞ ታጣቂዎች ወደ አገር በሚገቡበት ወቅት ህዝቡ ያሳያቸው ፍቅር በየመንገዱ ያደረገላቸው አቀባበል የሚደነቅ መሆኑን ነው የተናገሩት።

መንግስት በቅርቡ የአገሪቷን የፖለቲካ ምህዳር ለማስፋት በወሰዳቸው እርምጃዎች  በርካታ እስረኞች ተፈተዋል፣ በርካታ ሰዎች ከስደት ኑሮ ወደ አገር ተመልሰዋል።