የሚኒስትሮች ምክር ቤት በተለያዩ ርዕሰ ጉዳዮች ላይ ተወያይቶ ውሳኔዎችን አሳለፈ

137

ህዳር 3/2015(ኢዜአ) የሚኒስትሮች ምክር ቤት በዛሬው ዕለት ባካሄደው 15ኛ መደበኛ ስብሰባ በአራት ጉዳዮች ላይ ተወያይቶ ውሳኔ አሳለፈ፡፡

በሁሉም የአገሪቱ አካባቢዎች ሲካሄዱ የቆዩት ግጭቶች በሰላማዊ መንገድ የመጨረሻ እልባት እንዲያገኙ ማድረግ አስፈላጊ በመሆኑ፣ በተደራጀ ኃይል ውስጥ ታጥቀው ሲንቀሳቀሱ የነበሩ ኃይሎች ትጥቃቸውን ፈትተው ወደ ማህበረሰቡ በዘላቂነት እንዲቀላቀሉና ሰላማዊ ኑሮ መምራት እንዲችሉ ለማድረግ፣ በአገሪቱ የልማት፣ የሰላም እና የዲሞክራሲ ግንባታ ሂደት እንዲሳተፉ ለማስቻል ብሔራዊ የተሃድሶ ኮሚሽን ማቋቋም አስፈላጊ በመሆኑ ረቂቅ ደንብ ተዘጋጅቶ ለምክር ቤቱ ቀርቧል፡፡

ምክር ቤቱም በደንቡ ላይ በሰፊው ከተወያየ በኋላ ግብዓቶችን በማከል ከጸደቀበት ቀን ጀምሮ በስራ ላይ እንዲውል ወስኗል፡፡

መከላከያ ሠራዊቱ ከፖለቲካ ወገንተኝነት ነፃ ሆኖ የአገርን ሉአላዊነትና የዜጎችን ደህንነት የመጠበቅ ተልዕኮውን በአስተማማኝ ሁኔታ እንዲወጣ የሚያስችል የሪፎርም ስራ ውስጥ እንደሚገኝ፣ በዚህም አመርቂ ውጤቶች እየተመዘገቡ እንደሆነ ይታወቃል፡፡

ይህንን ሪፎርም የበለጠ ለማጎልበት እና ዘላቂነቱን ለማረጋገጥ ይቻል ዘንድ ከመከላከያ ሠራዊቱ ወቅታዊ እና የወደፊት ግዳጆች ጋር የሚጣጣም የህግ ማዕቀፍ በማስፈለጉ በሥራ ላይ ያለውን አዋጅ የሚተካ ረቂቅ አዋጅ ተዘጋጅቶ ለሚኒስትሮች ምክር ቤት ቀርቧል፡፡

ምክር ቤቱም በረቂቅ አዋጁ ላይ በሰፊው ከተወያየ በኋላ ግብዓቶችን በማከል ይጸድቅ ዘንድ ወደ ህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በሙሉ ድምጽ እንዲተላለፍ ወስኗል፡፡

የኢትዮጵያ ኢንተርፕራይዝ ልማት አደረጃጀት፣ ስልጣንና ተግባር ለመወሰን በቀረበ ረቂቅ ደንብ ላይም ምክር ቤቱ ተወያይቷል፡፡

የአምራች ኢንተርፕራይዝ ዘርፍ ተወዳዳሪነትን በማሳደግ የኢኮኖሚ መዋቅራዊ ሽግግር እንዲፋጠን ችግር ፈቺ የአቅም ግንባታ፣ የፋይናንስ፣ የማምረቻ መሳሪያ፣ የቴክኖሎጂ፣ የምክር አገልግሎት፣ የማምረቻ ቦታና መሰረተ-ልማት፣ የግብዓትና የገበያ ትስስር ድጋፎች በመስጠት ማኑፋክቸሪንግ ኢንተርፕራይዞችን የማስፋፋትና የማሸጋገር ተልዕኮ ያለው ተቋም በማስፈለጉ የኢትዮጵያ ኢንተርፕራይዝ ልማትን አደረጃጀት፣ ስልጣንና ተግባር ለመወሰን ረቂቅ ደንብ ተዘጋጅቶ ለሚኒስትሮች ምክር ቤት ቀርቧል፡፡

ምክር ቤቱም በረቂቅ ደንቡ ላይ በሰፊው ከተወያየ በኋላ ግብዓቶችን በማከል በነጋሪት ጋዜጣ ታትሞ ከወጣበት ቀን ጀምሮ በስራ ላይ እንዲውል ወስኗል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም