ጉባዔው የህወሓትን ጥንካሬና ድክመት በመለየት ውሳኔዎች የሚተላለፉበት እንደሚሆን ይጠበቃል - የኢህአዴግ አጋር ድርጅቶች

54
መቀሌ መስከረም 16/2011 የህወሓት 13ኛ ጉባኤ የድርጅቱን መልካም እሴቶችና ጥንካሬዎች የሚያስቀጥሉ ውሳኔዎች የሚተላለፉበት እንደሚሆን እምነት እንዳላቸው የኢህአዴግ አጋር ድርጅቶች ገለጹ። መቀሌ ላይ በተጀመረው የድርጅቱ ጉባኤ መክፈቻ የአፋር ብሔራዊ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ /አብዴፓ/፣ የሐረሪ ብሔራዊ ሊግ /ሐብሊ/ እና የቤኒሻንጉል ጉምዝ ህዝቦች ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ /ቤጉህዴፓ/ ተወካዮች መልዕክት አስተላልፈዋል። የአብዴፓ ተወካይ ህወሓት ኢህአዴግ ባለፉት ዓመታት በኢኮኖሚያዊ፣ ፖለቲካዊና ማህበራዊ ጉዳዮች ከትግራይ ባለፈ እንደ አገር ያመጣው እድገት ከፍተኛ ነው ብለዋል። በአፋርና በትግራይ ክልሎች ባለው የልማት ትብብር አመርቂ የልማት ተግባራት መከናወናቸውንም ተናግረዋል። በአሁኑ ወቅት በአገሪቱ የመጣውን ለውጥ ከዳር ለማድረስ 13ኛው ታሪካዊ ጉባኤ ከፍተኛ ሚና እንደሚጫወት አንስተዋል። በጉባኤው የሚተላለፉ ውሳኔዎችና አቅጣጫዎች የአገሪቱን ሰላምና አንድነት እንደሚያጠናክር ያላቸውን እምነትም ገልጸዋል። 13ኛው ጉባኤ ያለፉትን የድርጅቱን ድክመቶች ነቅሶ በማውጣትና ድርጅቱ የሚታወቅባቸውን ጥንካሬዎች በመለየት ጠንካራ ውሳኔዎች የሚተላለፉበት እንደሚሆን እምነት አለን ያሉት ደግሞ የሐረሪ ብሔራዊ ሊግ /ሐብሊ/ ተወካይ ናቸው። ድርጅቱ በጉባኤው የሚያስቀምጣቸውን ውሳኔዎችና አቅጣጫዎች አስመልክቶ የሐረሪ ብሔራዊ ሊግ ለተግባራዊነቱ በጋራ እንደሚሰራም ገልጸዋል። የቤኒሻንጉል ጉምዝ ህዝቦች ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ /ቤጉህዴፓ/ ተወካይም በአገሪቱ ለተመዘገበው የልማትና የዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ የህወሓት ሚና የላቀ መሆኑን አስታውሰዋል። በአሁኑ ወቅት አገሪቱ በለውጥ ምዕራፍ ላይ በመገኘቷና ከጎረቤት አገራት ጋር ያላትን ግንኙነት በተለየ መልኩ አጠናክራ በመቀጠሏ ጉባኤውም ይህንኑ ለውጥ የሚያጠናክሩ ውሳኔዎችን እንደሚያስተላልፍ ይጠበቃል ብለዋል። በተለይም ከኤርትራ ህዝብ ጋር ያለውን ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ግንኙነት ከማደስ ባለፈ የአገራቱን ወንድማዊ ግንኙነት ወደተሻለ ምዕራፍ ማሸጋገርም እንዲሁ። አገራዊ የፖለቲካ ምህዳሩን ለማስፋት እየተደረጉ ባሉ የለውጥ እንቅስቃሴዎች የህወሓት ሚና ተጠናክሮ የሚቀጥልባቸው ውሳኔዎችና አቅጣጫዎች እንደሚጠበቁም ተናግረዋል። መቀሌ ላይ የተጀመረው 13ኛው የህወሓት ድርጅታዊ ጉባኤ "የአንድነትና የጽናት ጉባኤ ለህዳሴያችን" በሚል መሪ ሃሳብ ነው የሚካሄደው።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም