ምሁራን በየሔዱበት ቦታ ሁሉ ስለሃገር ሰላምና ስለ ህዝብ አንድነት ሊያስተምሩ ይገባል--የወሎ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት

137

ደሴ (ኢዜአ) ህዳር 3/2015 በተለያዩ የትምህርት ዘርፎች ከዩኒቨርሲቲ የሚመረቁ ምሁራን በሄዱበት ቦታ ሁሉ ስለ ሰላምና ስለ ሃገር አንድነት ሊያስተምሩ እንደሚገባ የወሎ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት ዶክተር መንገሻ አየነ አሳሰቡ።

ወሎ ዩኒቨርሲቲ በተለያየ መርሐ ግብር በመጀመሪያና በሁለተኛ ዲግሪ ያሰለጠናቸውን ከ6 ሺህ በላይ ተማሪዎች በኮምቦልቻ ካምፓስ ዛሬ እያስመረቀ ነው።

ዩኒቨርሲቲው ለ14ኛ ጊዜ ዛሬና ነገ ከሚያስመርቃቸው መካከል አንድ ሺህ 744ቱ ሴቶች ናቸው።

በምረቃ መርሃ-ግብሩ ላይ የዩኒቨርሲቲው ፕሬዝዳንት ዶክተር መንገሻ አየነ እንደገለፁት ዩኒቨርሲቲው ብቁ፣ ተወዳዳሪ ፣ አምራችና ስራ ፈጣሪ ትውልድ ለማፍራት እየሰራ ነው።

በመደበኛ፣ በክረምት፣ በተከታታይና በርቀት መርሐ ግብር ያሰለጠናቸው ተመራቂዎች በዩኒቨርሲቲ ቆይታቸው የቀሰሙትን እውቀትና ልምድ ተጠቅመው ስራ ጠባቂ ሳይሆኑ ስራ ፈጣሪ ሊሆኑ እንደሚገባም አሳስበዋል።

በሚሄዱበትና በሚያገኙት አጋጣሚ ሁሉ ስለ ሰላምና አንድነት እየሰበኩ ለኢትዮጵያ ዘላቂ ሰላምና አንድነትም የድርሻቸውን እንዲወጡ መልዕክት አስተላልፈዋል።

የዕለቱ የክብር እንግዳ የሀገር መከላከያ ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር አህመዲን መሃመድ በበኩላቸው፣ ምሩቃን በርካታ ውስብስብ ፈተናዎችን አልፈው ለዛሬዋ ቀን መድረሳቸው ገልጸዋል።

በቀጣይ በሰለጠኑበት የሙያ ዘርፍ ሀገራቸውንና ህዝባቸውን በታማኝነትና በታታሪነት እንዲያገለግሉ አስገንዝበዋል።

የኢትዮጵያን ሰላምና አንድነት ለማስጠበቅ በሚደረገው ጥረት የበኩላቸውን እንዲወጡም ነው ዶክተር አህመዲን ያመለከቱት።

ከምሩቃን መካከል በሲቪል ኢንጅሪንግ የተመረቀው ሀብታሙ ሙጨ በሰጠው አስተያየት ብዙ ውጣ ውረድ አልፎ ለዛሬ ቀን በመብቃቱ መደሰቱን ገልጿል።

በዩኒቨርሲቲ ቆይታው የቀሰመውን እውቀትና ልምድ ተጠቅሞ ሀገርና ህዝብን በታማኝነት ከማገልገል ባለፈ ለህዝቦች ዘላቂ ሰላምና አንድነት የበኩሉን እንደሚወጣ አረጋግጧል።

"የመንግስት ሥራን ብቻ ሳልጠብቅ የራሴን ሥራ በመፍጠር ከቤተሰብ ጥገኝነት ለመላቀቅ የምችለውን ሁሉ አደርጋለሁ" ያለችው ደግሞ በኮምፒውተር ሳይንስ የትምህርት መስክ የተመረቀችው ሰዓዳ የሱፍ ናት።

በምርቃት መርሃግብሩ ላይ የመከላከያ ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር አህመዲን መሃመድን ጨምሮ የዩኒቨርሲቲው አመራሮች፣ የተማሪ ወላጆች፣ ምሩቃን ተማሪዎችና ሌሎችም ባለድርሻ አካላት ተገኝተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም