ወቅቱን ያልጠበቀ ዝናብ በደረሱ ሰብሎች ላይ ጉዳት እንዳያደርስ አርሶ አደሩ ጥንቃቄ ሊያደርግ ይገባል - የግብርና ሚኒስቴር

156

አዲስ አበባ ህዳር 2/2015/ኢዜአ/ ወቅቱን ያልጠበቀ ዝናብ በደረሱ ሰብሎች ላይ ጉዳት እንዳያደርስ አርሶ አደሩ ጥንቃቄ ሊያደርግ እንደሚገባ የግብርና ሚኒስቴር አሳሰበ።

በ2014/15 ዓ.ም የመኸር ምርት ዘመን 400 ሚሊዮን ኩንታል ምርት ለመሰብሰብ እየተሰራ እንደሚገኝም ሚኒስቴሩ አስታውቋል።

የግብርና ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር መለሰ መኮንን ለኢዜአ እንደገለጹት በተያዘው በ2014/2015 ዓ.ም የመኸር ምርት ዘመን  ከተሸፈነ 13 ነጥብ4 ሚሊዮን ሄክታር መሬት  400 ሚሊዮን ኩንታል ምርት ለመሰብሰብ እየተሰራ ነው።

በአገሪቱ በቆላማ፣ ሞቃታማና መካከለኛ ቦታዎች ላይ ሰብል እየተሰበሰበ እንደሚገኝ ተናግረው በደጋማው አካባቢ ሰብል በመድረሰ ላይ እንዳለም ጠቁመው ።

በተያዘው የመኸር ወቅትም ከማሳ ዝግጅት እስከ ሰብል አሰባሰብ ባሉት ወራቶች  ምርታማነትን ለማሳደግ ልዩ ትኩረት ተሰጥቶ ሲሰራ መቆየቱን ጠቅሰዋል።

የግብርና ሚኒስቴርም የምርት ብክነትን ለመቀነስም ጤፍ፣ አኩሪ አተር፣ ስንዴን ጨምሮ በተለያዩ ቦታዎች ላይ ከ1 ሺህ 500 በላይ ኮንባይነሮችን በማሰማራት ምርት እየተሰበሰበ እንዳለ ተናግረዋል።

በአሁኑ ወቅትም በተለያዩ የአገሪቱ አካባቢዎች ወቅቱን ያልጠበቀ ዝናብ እየጣለ እንደሚገኝ ጠቁመዋል።

የብሔራዊ ሚቲዎሮሎጂ ኢንስትቲዩት ትንበያ እንደሚያመለክተው በሚቀጥሉ ቀናት በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች ወቅቱን ያልጠበቀ ዝናብ ሊቀጥል  እንደሚችል አስታውቋል።

በደረሰ ምርት ላይ ዝናብ ጉዳት እንዳያደርስ አርሶ አደሩ፣ የግብርና ባለሙያው እና በየደረጃው የሚገኝው አመራር በልዩ ትኩረት ሊሰራ እንደሚገባ አስገንዝበዋል።

ኢትዮጵያ ስንዴን በስፋት በማምረት  ከራስ አልፎ ወደ ውጭ ለመላክ የያዘችውን እቅድ እውን ለማድረግም ሰፊ የግብርና ልማት ስራ እየተካሄደ እንደሚገኝም ሚኒስትር  ዴኤታው  አስታውቀዋል።

በተያዘው የመኸር ወቅትም በኩታ ገጠም የአስተራረስ ዘዴ የተካሄደው የስንዴ ሰብል በተሻለ ቁመና ላይ እንደሚገኝ ጠቁመዋል።

የመኸር ሰብል ከመሰብሰብ ጎን ለጎንም በ1 ነጥብ 3 ሚሊዮን ሄክታር መሬት ላይ 52 ሚሊዮን ኩንታል ስንዴን በበጋ በመስኖ ለማልማት ወደ ተግባር መገባቱን አስታውቀዋል።

በመስኖ ስንዴ በሚያለሙ ቆላማ፣ መካከለኛና ደጋማ አካባቢዎችም የማሳ ዝግጅትን ጨምሮ የአቅም ግንባታ ስልጠና፣ የማዳበሪያና የግብዓት አቅርቦት ተደራሽ እየተደረገ እንደሚገኝ ተናግረዋል።

በተያዘው የመኸር ወቅት ስንዴ አሰባሰብ ላይም የህብረት ስራ ማህበራትን ጨምሮ ተማሪዎች፣ የግብርና ሙያተኞችና ልዩ ልዩ የማህበረሰብ ክፍሎች ተሳትፎ በማድረግ በዘመቻ የሰብልን ብክነት ቀድሞ መከላከል እንደሚገባ ጥሪ ቀርቧል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም