የህዳሴው ግድብ የሚያመጣውን የኢንቨስትመንት አማራጮች ለመጠቀም እየተሠራ ነው -ቢሮው

107

አሶሳ /ኢዜአ/ ህዳር 02 / 2015  ፡- በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል የህዳሴው ግድብ የሚያስገኛቸውን የኢንቨስትመንት አማራጮች ለመጠቀም እየተሰራ መሆኑን የክልሉ ገጠር መሬት አስተዳደር እና ኢንቨስትመንት ቢሮ አስታወቀ።

የክልሉ ከፍተኛ አመራሮች በክልሉ የገጠር መሬት አስተዳደር እና አጠቃቀም አዋጅ ማስፈጸሚያ ረቂቅ ደንብ ላይ ዛሬ ተወያይተዋል፡፡

የክልሉ ገጠር መሬት አስተዳደር እና ኢንቨስትመንት ቢሮ ሃላፊ አቶ አመንቴ ገሺ በወቅቱ እንደተናገሩት የህዳሴው ግድብ በክልሉ ከፍተኛ የኢንቨስትመንት አማራጮችን ይዞ ይመጣል፡፡

"ክልሉ ካለው የኢንቨስትመንት አማራጮች ውስጥ አንዱና ዋነኛው ለም መሬት ነው" ያሉት ሃላፊው ሃብቱ በተለይም በሙስና፣ ቢሮክራሲያዊ አሰራርና በሌሎች ማነቆዎች ሳቢያ ሳይለማ ቆይቷል" ብለዋል፡፡

የዘርፉን ፈተናዎች በመቅረፍ በተለይም በህዳሴው ግድብ አካባቢ የሚፈጠረውን የኢንቨስትመንት አማራጭ ለመጠቀም ቢሮው በ2015 በጀት አመት የኢንቨስትመንት ዘርፉ ላይ ጠንካራ ማሻሻያ ማድረግን ትኩረት አድርጎ እየሠራ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

ለዚህ ደግሞ የቢሮውን መዋቅር በማስተካከል በሰው ሃይል በማደራጀት ማነቆ የሆነ ቢሮክራሲን ለመቀነስ አገልግሎት አሰጣጡን የበለጠ ለማዘመን የሚደረግ ጥረት መኖሩን አስረድተዋል፡፡

እንዲሁም መንገድን ጨምሮ ወሳኝ መሠረተ ልማቶችን ማስፋፋት ሌላው ዋነኛ ጉዳይ እንደሆነ የገለጹት አቶ አመንቴ "ህብረተሰቡ ከኢንቨስትመንቱ ቀጥተኛ ተጠቃሚ እንዲሆን ይደረጋል" ብለዋል፡፡

በ2014 በጀት ዓመት የኢንቨስትመንት መሬት ወስደው ካላለሙ 37 ከፍተኛ ፕሮጀክቶችን ፍቃድ በመሰረዝ የወሰዱትን መሬት እንዲመልሱ መደረጉን አመልክተዋል፡፡

በተያዘው በጀት አመት ኢንቨስትመንቱን ለማሻሻል ሲባል በገቡት ውል መሠረት በማይሰሩ ባለሃብቶች ላይ የሚወሰደው እርምጃ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ጠቁመው አፈጻጸማቸውን መሠረት በማድረግ እርምጃ የሚወሰድባቸውን ባለሃብቶች የመለየት ስራ እየተከናወነ መሆኑን አስታውቀዋል፡፡

በክልሉ የገጠር መሬት አስተዳደርና አጠቃቀም አዋጅ ማስፈጸሚያ ረቂቅ ደንብን ያቀረቡት በቢሮው የህግ ረቂቅ ባለሙያ አቶ ታደሰ በየነ በበኩላቸው አዋጁን ለማስፈጸም የተዘጋጀው ረቂቅ ደንቡ ባለሃብቶች ከዚህ ቀደም ለኢንቨስትመት የሚረከቡትን መሬት እስከ 40 ዓመት የሚይዙበትን አሰራር እንደሚያስቀር ጠቁመዋል፡፡

ደንቡ ባለሃብቶች የሚወስዱትን መሬት የሚጠቀሙት እስከ 25 ዓመት እንደሆነ ጠቁመው "በየአምስት ዓመቱ የአካባቢ ጥበቃ መሠረት አድርገው መስራታቸው ተገምግሞ ውጤታማ ሲሆኑ ብቻ እንደሚቀጥሉ ያስገድዳል" ብለዋል፡፡

በዚሁ መሠረት የማይሠሩ ባለሃብቶች ውላቸው እንዲቋረጥ ደንቡ እንደሚደነግግ ባለሙያው አስረድተዋል፡፡

እንዲሁም የአርሶ አደሩ የመሬት ባለቤትነት መብትና ሌሎች የተፈጥሮ ሃብቱን በሚገባ ማልማት በሚያስችሉ ጉዳዮችን በሚገባ በሚያጠናክር መልኩ ደንቡ እየተዘጋጀ መሆኑን ባለሙያው አስታውቀዋል፡፡

የአዋጁ ማስፈጸሚያ ደንብ  በአንድ ወር ጊዜ ውስጥ በክልሉ ካቢኔ እንደሚጸድቅ በወቅቱ ተመላክቷል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም