የኢትዮጵያና የሶማሊያ የመረጃና ደህንነት ተቋማት የአልሸባብን የሽብር ጥቃት በጋራ ለመከላከል ተስማሙ

112

ህዳር 2/2015 (ኢዜአ) የኢትዮጵያና የሶማሊያ የመረጃና ደህንነት ተቋማት የአልሸባብን የሽብር ጥቃት በጋራ ለመከላከል መስማማታቸውን የብሄራዊ መረጃ ደህንነት አገልግሎት አስታወቀ ።

በሶማሊያ ላይ በተደጋጋሚ የሽብር ጥቃቶችን በመፈፀም የሚታወቀው የአልሸባብ የሽብር ቡድን ሰሞኑን በሞቃዲሾ የሽብር ጥቃት በመፈፀም በሰው ሕይወትና በንብረት ላይ ከፍተኛ ጉዳት ማድረሱ ይታወቃል፡፡

ይህ የሽብር ቡድን ባለፈው ዓመትም ሐምሌ 13/2014 ዓ.ም. ወደ ኢትዮጵያ ድንበር ዘልቆ በመግባት በመለመላቸው ፣ ባደራጃቸውና ስምሪት በሰጣቸው አባላቱ ጥቃት ከፍቶ በተሰነዘረበት የአፃፋ ምት ከፍተኛ ኪሳራ መከናነቡም ይታወሳል።

በመሆኑም የኢትዮጵያና የሶማሊያ አቻ የመረጃና ደህንነት ተቋማት የአፍሪካ ቀንድ ስጋት የሆነውን አልሻባብን ለመከላከልና የሽብር እንቅስቃሴውን ለመግታት የሚያስችል የተቀናጀ የመረጃ ልውውጥና የጋራ ኦፕሬሽን ለማካሄድ የሚያስችል የመግባቢያ ሰነድ መፈራረማቸውን የብሄራዊ መረጃ ደህንነት አገልግሎት ለመገናኛ ብዙሃን በላከው መረጃ አመልክቷል፡፡

የመግባቢያ ሰነዱን የተፈራረሙት የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት ዳይሬክተር ጀነራል አቶ ተመስገን ጥሩነህ እና የሶማሊያ የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት ኤጀንሲ ዳይሬክተር ጀነራል ማሀድ ሞሐመድ መሆናቸውን አገልግሎት መስሪያ ቤቱ አስታውቋል፡፡

የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት ዳይሬክተር ጀነራል አቶ ተመስገን ጥሩነህ በስምምነቱ ወቅት አልሸባብ በቅርቡ በሞቃድሾ ከተማ በፈፀመው የሽብር ጥቃት እጅግ ማዘናቸውን ገልጸዋል።

የሽብር ቡድኑ ለኢትዮጵያና ሶማሊያ ብቻ ሳይሆን ለአፍሪካ ቀንድም የስጋት ምንጭ በመሆኑ ተቋማቸው የቡድኑን የግንኙነት መረብ ሲያጠና መቆየቱንና አሁንም በቡድኑ አባላት ላይ ጥብቅ ክትትል እያደረገ መሆኑን አስረድተዋል።

የብሄራዊ መረጃ ደህንነት አገልግሎት ከሶማሊያ የመረጃና ደህንነት ተቋማት ጋር የመረጃ ልውውጦችን በማድረግም በተመረጡ ቦታዎች በኦፕሬሽን ስራዎች በመሳተፍ እንደሚያግዝና ዘርፈ ብዙ ድጋፎችንም እንደሚያደርግ አመልክተዋል።

የሶማሊያ የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት ኤጀንሲ ዳይሬክተር ጀነራል ማሀድ ሞሐመድ በበኩላቸው የአልሸባብ የሽብር ቡድን ከሶማሊያም አልፎ ኢትዮጵያን ጨምሮ በአካባቢው ሃገራትም ጭምር ድንበር ተሻግሮ ጥቃት በመሰንዘር ለአፍሪካ ቀንድ የሚፈጥረው ስጋት እያደገ መምጣቱን ገልጸዋል።

ቡድኑ በአካባቢው የሚፈጥረውን ስጋት ለማስቀረት በሶማሊያና ኢትዮጵያ ውስጥ የሚንቀሳቀሱትን የሽብር ቡድኑ መሪዎችና ሴሎችን በጋራ በማጽዳት በኩል የኢትዮጵያና የሶማሊያ አቻ የመረጃና ደህንነት ተቋማት ከመቼውም ጊዜ በላይ ተቀናጅተው መሥራት ይገባቸዋል ብለዋል።

ኢትዮጵያ ሽብርተኝነትን የመከላከልና የማምከን ከፍተኛ አቅምና ልምድ እንዳላት የገለጹት የሶማሊያ የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት ኤጀንሲ ዳይሬክተር ጀነራል የሁለቱ ሀገራት የጋራ ጠላት የሆነውን የአልሸባብን የሽብር ቡድን እንቅስቃሴ ለመግታት በመረጃ ልውውጥ ፣የተቀናጀ ፀረ አልሸባብ ኦፕሬሽን ስምሪት በመውሰድና ቀጠናዊ ዘላቂ ሰላምና ደህንነትን በማረጋገጥ በኩል የተደረሰውን የትብብር ስምምነት ተግባራዊ በማድረግ ውጤት እንደሚመዘገብ ከወዲሁ እምነታቸው መሆኑን ገልጸዋል።

በኢትዮጵያ በመረጃና ደኅንነት ተቋማት በሚካሄዱት ተቋማዊ የሪፎርም ሥራዎችና ተቋሙ በፈጠረው አቅም እጅግ መደነቃቸውንና በኢትዮጵያ የተመለከቱትን የተቋማት ሪፎርም የኢትዮጵያ ድጋፍ ተጨምሮበት በሶማሊያም ተግባራዊ በማድረግ በሀገራቸው ፀጥታና ደህንነት እንዲረጋገጥ ትኩረት ሠጥተው እንደሚሠሩ ተናግረዋል።

በሶማሊያ የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት ኤጀንሲ ዳይሬክተር ጀነራል ማሀድ ሞሐመድ የተመራው የሶማሊያ የመረጃና ደኅንነት ተቋም የልዑካን ቡድን የብሄራዊ መረጃና ደኅንነት ዩኒቨርስቲ ኮሌጅን የጎበኘ ሲሆን በዩኒቨርስቲ ኮሌጁ ስለሚሠጠው የንድፈ ሃሳባዊና የተግባር ሥልጠና እንዲሁም በዲግሪና በማስተርስ መርሃ ግብሮች የጀመራቸውን ሥልጠናዎች በተመለከተ ማብራሪያ ተደርጎለታል ።

የብሄራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት ለመገናኛ ብዙሃን በላከው መረጃ ኢትዮጵያና ሶማሊያ ረጅም የድንበር ወሰን የሚጋሩ ሲሆን ተመሳሳይ ባህል ፣ ቋንቋና ሃይማኖት ያላቸው በተለያዩ ሀገራት የሚኖሩ ቢሆንም አንድ ህዝቦች መሆናቸውን አመልክቷል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም