የብሔር ብሔረሰቦች በዓል እንግዶችን ተቀብሎ ለማስተናገድ የሀዋሳ ከተማ ነዋሪዎች ቅድመ ዝግጅት እንዲያደርጉ ተጠየቀ

125

ሀዋሳ (ኢዜአ) ህዳር 2/2015  ኢትዮጵያዊነትን በማጉላት ህዳር 29 ለሚከበረው የብሔር ብሔረሰቦች ቀን በዓል እንግዶችን በአክብሮት ተቀብሎ ለማስተናገድ የሀዋሳ ከተማ ነዋሪዎች ከወዲሁ ዝግጅት እንዲያደርጉ የከተማዋ አስተዳደር ከንቲባ ረዳት ፕሮፌሰር ፀጋዬ ቱኬ ጥሪ አቀረቡ።


የብሔር ብሔረሰቦችን ቀን በዓል አከባበር ዝግጅትን አስመልክቶ የሀዋሳ ከተማ ከንቲባ ረዳት ፕሮፌሰር ፀጋዬ ቱኬ ከከተማዋ ነዋሪዎች ጋር መክረዋል።

የታላቋ ኢትዮጵያ ነጻብራቅና የብሔር ብሔረሰቦች መኖሪያ በሆነችው ሀዋሳ ህዳር 29 የሚከበረውን 17 ኛውን የብሔር ብሔረሰቦች ቀን በዓል ታስተናግዳለች።

ከንቲባ ረዳት ፕሮፌሰር ፀጋዬ በውይይቱ እንዳነሱት ለበዓሉ የሚመጡ "ኢትዮጵያዊያን ወደ ቤታቸው ነው የሚመጡት"።

የከተማዋ ነዋሪዎች ታዲያ እንግዶችን በቆየው ኢትዮጵዊ ክብር ተቀብለው ለማስተናገድ በቂ ዝግጅት ማድረግ ይጠበቅባቸዋል።

በዚህ ረገድ ከተማ አስተዳደሩ በርካታ የቅድመ ዝግጅት ሥራዎችን እያከናወነ መሆኑን የጠቀሱት ካንቲባው፤ በተለይም የእንግዶችን ደህንነት አስተማማኝ ለማድረግ የሚያስችል የጸጥታና የሰላም ማስጠበቅ ሥራዎችን ለአብነት አንስተዋል።

ህብረተሰቡም የተለመደውን ትብብር በማሳየት የሀዋሳን እንግዳ ተቀባይነትና ተመራጭ ከተማነት ዳግም ሊያረጋግጥ እንደሚገባ ጥሪ አቅርበዋል።

ከተማዋን ይበልጥ ውብና ፅዱ ማድረግ፣ የትኛውንም ዓይነት ሕገወጥ እንቅስቃሴንና ያልተገባ የሸቀጦችና የአገልግሎት የዋጋ ጭማሪን በመከላከል በኩል ህብረተሰቡ ተባብሮ በመስራት ሃላፊነቱን ሊወጣ እንደሚገባ በማመላከት። 

"ሀዋሳ በብዙ መንገድ ለሌሎች ከተሞች ተሞክሮ የሚቀስሙባት ከተማ መሆኗን አጉልተን ለማሳየት በቂ ዝግጅት ማድረግ ከያንዳንዳችን ይጠበቃልም" ብለዋል።

ከነዋሪዎቹ መካከል ሼህ ከሊል ሸምሰዲን ሀዋሳ የብሔር ብሔረሰቦችን ቀን ለማዘጋጀት በመመረጧ እጅግ ደስተኛ መሆናቸውን ጠቅሰው፣ "ከተማችንን ይበልጥ የምናሳይበት መልካም ዕድል ነው" ብለዋል።

ለእንግዶቻችን ተገቢውን ክብርና ፍቅር በማሳየት በከተማዋ የሚኖራቸው ቆይታ ይበልጥ አስደሳች እንዲሆን ኃላፊነታችንን እንወጣለን ነው ያሉት።

ወይዘሮ መርከብ ማሞ በበኩላቸው "እንግዶቻችንን በክብር ከመቀበል ጀምሮ የአካባቢያችንን ፀጥታ በመጠበቅ ይበልጥ ደህንነት እንዲሰማቸውና ሀዋሳን እንዲወዷት ለማድረግ ተዘጋጅተናል" ብለዋል።

ሀዋሳ ሁሉም ብሔር ብሔረሰቦች በፍቅር የሚኖሩባት ከተማ መሆኗን አውስተው፣ እንግዶች በከተማዋ በልበ ሙሉነት እንዲንቀሳቀሱ የሚያደርግ ቤተሰባዊ አቀባበል እንደሚያደርጉላቸው ተናግረዋል።

በውይይቱ ላይ ከንቲባውን ጨምሮ በብልፅግና ፓርቲ የሀዋሳ ከተማ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ካሱ አሩሳ እና ሌሎች የመንግስት የሥራ ሃላፊዎች ተገኝተዋል።

በየዓመቱ ህዳር 29 በታላቅ ድምቀት የሚከበረው የብሔር ብሔረሰቦች ቀን ዘንድሮ ለ17ኛ ጊዜ የሚከበር ሲሆን በዓሉን እንድታዘጋጅ የተመረጠችው ሀዋሳ ከተማ የተለያዩ የቅድመ ዝግጅት ሥራዎችን እያከናወነች ትገኛለች።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም