ኮሚሽኑ ለውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት ምቹ ሁኔታ ለመፍጠር ከክልሎች ጋር ተቀናጅቶ ሊሰራ ይገባል--ቋሚ ኮሚቴው

160

አዲስ አበባ (ኢዜአ) ህዳር 2/2015 የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን ለውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት ምቹ ሁኔታ ለመፍጠር ከክልሎች ጋር ተቀናጅቶ ሊሰራ እንደሚገባ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አሳሰበ።

የምክር ቤቱ የንግድና ቱሪዝም ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ፤ የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽንን የ2015 በጀት ዓመት የመጀመሪያ ሩብ አመት እቅድ አፈጻጸምን ገምግሟል።

የኮሚሽኑን የመጀመሪያ ሩብ ዓመት አፈጻጸም አስመልክቶ ሪፖርት ያቀረቡት ኮሚሽነሯ ለሊሴ ነሜ፤ በሩብ ዓመቱ ከውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት ዘጠኝ መቶ ሚሊዮን ዶላር መሳብ መቻሉንም  ጠቅሰዋል፡፡

ይህም 67 በመቶ አፈጻጸም እንዳለው ጠቅሰው፤ ተቀያያሪ የሆነው የዓለም ጂኦ ፖለቲካና ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴ እንዲሁም በአገር ውስጥ የነበረው ሁኔታ እቅዱ በሚፈለገው ደረጃ እንዳይተገበር እንቅፋት መፍጠሩን ተናግረዋል፡፡

በሩብ ዓመቱም ከኢንቨስትመንት ዘርፍ ለ13 ሺህ ዜጎች የስራ ዕድል መፈጠር መቻሉን ጠቁመው በቀጣይ አፈጻጸሞቹን ከፍ ለማድረግ የሚሰራ መሆኑንም ጠቁመዋል፡፡

የቋሚ ኮሚቴ ምክትል ሰብሳቢ አሰማኸኝ አስረስ፤ ኮሚሽኑ ከተሰጠው ተልእኮ አንጻር በሩብ አመቱ ያስመዘገበው ውጤት የሚፈለገውን ያህል አለመሆኑን ገልጸዋል።

በመሆኑም ኮሚሽኑ በቀጣይ የተለዩ አቅጣጫዎችን በማስቀመጥ የአፈጻጸም ጉድለቱን የማካካስ ስራ እንዲያከናውን አስገንዝበዋል፡፡

የቋሚ ኮሚቴው ሰብሳቢ አሻ ያህያ፤  ኮሚሽኑ በቀጣይ ኢንቨስትመንትን ለመሳብ የሚያስችሉ ምቹ ሁኔታዎችን የመፍጠር ስራ ላይ ትኩረት ሊያደርግ ይገባል ብለዋል፡፡

የአፈጻጸም ክፍተቶች በአግባቡ በመለየት ፣ አሰራርን በማዘመን፣ ከሚመለከታቸው የክልልና የከተማ አስተዳደሮች ጋር በመወያየት የዘርፉን ማነቆ መፍታት እንደሚገባም አሳስበዋል።

ኮሚሽኑ ከቋሚ ኮሚቴው የተሰጡትን ገንቢ ሃሳቦች በመውሰድ በቀጣይ የላቀ ውጤት ለማስመዝገብ እንደሚሰራም አረጋግጧል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም