የኤሌክትሪክ እና የባንክ አገልግሎት ዳግም መጀመሩ ከእንግልት እና ወጭ ታድጎናል---የፅፅቃ ከተማ ነዋሪዎች

122

ሰቆጣ (ኢዜአ) ህዳር 2/2015 በዋግኽምራ ብሔረሰብ አስተዳደር ዝቋላ ወረዳ ፅፅቃ ከተማና አካባቢው ለ15 ወራት ተቋርጦ የነበረው የኤሌክትሪክና የባንክ አገልግሎት በመጀመሩ መደሰታቸውን ነዋሪዎች ገለጹ።

በፅፅቃ ከተማ በንግድ ሥራ የተሰማሩት አቶ ሃይሌ መኮንን ለኢዜአ እንዳሉት የኤሌክትሪክና የባንክ አገልግሎት ለ15 ወራት በመቋረጡ ምክንያት ለተለያዩ ችግሮች ተዳርገው ቆይተዋል።

የኤሌክትሪክ አገልግሎቱ መቋረጡ በተሰማሩበት የምግብና መጠጥ ንግድ ሥራ ላይ ችግር መፍጠሩንም ነው የገለጹት።

ከእሳቸው በተጨማሪ በአካባቢያቸው በእንጨትና ብረታ ብረት ሥራ የተሰማሩ ወጣቶች በኤሌክትሪክ ሀይል አቅርቦት መቋረጥ ምክንያት ለችግር ተጋልጠው እንደነበር አስታውሰዋል።

የባንክ አገልግሎት በመቋረጡም እሳቸውን ጨምሮ የፅፅቃ ከተማና የዝቋላ ወረዳ ነጋዴዎች ከ60 እስከ 190 ኪሎ ሜትር ርቀው በመሄድ ሰቆጣና ጓህላ ከተሞች ከሚገኙ ባንኮች ገንዘብ ለማውጣት መገደዳቸውን ተናግረዋል።

በዚህም እርሳቸውን ጨምሮ የአካባቢው ነዋሪዎች ለእንግልትና ለውጭ ተዳርገው እንደነበር ጠቁመዋል።

"መንግስትና ህወሓት የሰላም ስምምነት ማድረጋቸውን ተከትሎ በፅፅቃ ከተማና አካባቢው ለ15 ወራት ተቋርጦ የነበረው የኤሌክትሪክና የባንክ አገልግሎት ዳግም በመጀመሩ ችግራችን ተፈቷል፤ በእዚህም ደስተኛ ነኝ" ብለዋል።

ወይዘሮ አስረስ ወርቁ የተባሉ ነዋሪ በበኩላቸው የኤሌክትሪክ አገልግሎት መቋረጥ በተለይ ሴቶችን ለእንግልት ዳርጎ እንደነበር አስታውሰዋል።

የኤሌክትሪክ ሃይል በመቋረጡ የማገዶ አንጨት በውድ ዋጋ ገዝተው ይጠቀሙ እንደነበርና የንፁህ መጠጥ ውሃ አቅርቦት ላይም ችግር ፈጥሮ እንደነበር ተናግረዋል።

በባንክ የተቀመጠን ገንዘብ አውጥቶ ለመጠቀም ባለመቻሉም እሳቸውን ጨምሮ ብዙ የከተማዋ ነዋሪዎች ለችግር ተዳርገው እንደነበር አስታውሰዋል።

"በአሁኑ ወቅት የኤሌክትሪክና የባንክ አገልግሎት ዳግም መጀመሩ በተለይ ሴቶች ላይ ሲደርስ የነበረውን ስቃይና እንግልት አቃሏል" ብለዋል።

የኤሌክትሪክ አገልግሎት መጀመሩ ወላድ እናቶች በጤና ተቋም የወሊድ አገልግሎት እንዲያገኙ በማድረግ በኩል አስተዋፅኦው የጎላ መሆኑንም ገልጸዋል።

"የባንክና የኤሌክትሪክ አገልግሎት በማግኘታቸው ደስተኛ መሆናቸውን የገለጹት ደግሞ በመንግስት ሥራ የተሰማሩት አቶ አለማየሁ እንደሻው ናቸው።

ከአንድ ዓመት በላይ የኤሌክትሪክ አገልግሎት መቋረጡ በሚሰሩበት የመንግስት ተቋማት ጭምር ህዝባዊ አገልግሎት ለመስጠት ተቸግረው እንደነበር ገልጸዋል።
"በአሁኑ ወቅት የኤሌክትሪክና የባንክ አገልግሎት ዳግም መጀመሩ የነበረባቸውን ችግር ከመፍታት ባለፈ በከተማዋ ተቋርጠው የነበሩ የተለያዩ ሥራዎች እንዲጀምሩ አድርጓል" ብለዋል።
መንግስት በጦርነቱ የተጎዱ መሰረተ ልማቶችን በመጠገን መልሶ ሥራ ለማስጀመር እያደረገ ባለው ጥረት በዋግኽምራ ብሔረሰብ አስተዳደር በሰቆጣ፣ ፅፅቃ እና መሸሃ ከተሞች የኤሌክትሪክ አገልግሎት ማግኘታቸው ይታወቃል።

------------

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም