በ122 ሺህ ሄክታር መሬት ላይ የለማው ሰሊጥ ወቅቱን ጠብቆ ተሰበሰበ

282

መተማ ህዳር 2/2015 (ኢዜአ) በ122 ሺህ ሄክታር መሬት  ላይ የለማው ሰሊጥ ወቅቱን ጠብቆ መሰብሰቡን የምዕራብ ጎንደር ዞን ግብርና መምሪያ አስታወቀ።

በመምሪያው የሰብል ልማትና ጥበቃ ቡድን መሪ አቶ ጌትነት ካሳሁን ለኢዜአ እንዳሉት የሰሊጥ ሰብሉ  በ400 ባለሃብቶችና 40ሺህ በሚጠጉ አርሶ አደሮች ማሳ ላይ የለማ ነው።

ሰብሉ ወቅቱን ባልጠበቀ ዝናብ ጉዳት እንዳይደርስበት ከ800 ሺህ በላይ የጉልበት ሰራተኞችን በመጠቀም ፈጥኖ መሰብሰብ መቻሉን ተናግረዋል።

ሰብሉ ከብክነት በፀዳ መንገድ መሰብሰቡን ጠቁመው ከተሰበሰበው ሰብል 800 ሺህ ኩንታል ምርት እንደሚጠበቅ አመላክተዋል።

ሰብሉ የምርት ጥራትን ታሳቢ ተደርጎ በመሰብሰቡም ለውጭ ገበያ በማቅረብ ሀገሪቱ የተሻለ ምንዛሬ እንድታገኝ የሚያግዛት መሆኑን  ቡድን መሪው አስታውቀዋል።

በአበበ ውለታው የእርሻ ልማት ድርጅት ስራ አስኪያጅ አቶ ዳዊት ውለታው በበኩላቸው በመኽር ወቅቱ በ60 ሄክታር መሬት ላይ ያለሙትን ሰሊጥ ከ1ሺህ በላይ የጉልበት ሰራተኞችን በመጠቀም ሙሉ በሙሉ መሰብሰባቸውን ተናግረዋል።

''የሰሊጥ ሰብሉ በፍጥነት እና በጥራት መሰብሰቡን ጠቁመው ከተሰበሰበው የሰሊጥ ሰብል ከ300 ኩንታል በላይ ምርት እንደሚጠብቁ አመላክተዋል ።

በመኽር ወቅቱ በ2 ሄክታር መሬት ላይ ካለሙት የሰሊጥ ሰብል 11 ኩንታል ምርት ማግኘታቸውን የገለጹት ደግሞ በመተማ ወረዳ ገንዳ ውሃ ብርሽኝ ቀበሌ ነዋሪ አርሶ አደር ንጉሴ ተሻገር ናቸው።

ዘንድሮ የተስተካከለ የዝናብ መጠን መኖሩና ወቅቱን በጠበቀ ጊዜ መሰብሰብ በመቻላቸው ባለፈው አመት በተመሳሳይ ማሳ  አልምተው ካገኙት በ3 ኩንታል ብልጫ ያለው ምርት ማግኘታቸውን ተናግረዋል።

''በዚህ ዓመት ያለው የገበያ ሁኔታም በጣም ተጠቃሚ አድርጎኛል'' ያሉት አርሶ አደሩ በኩንታል 9 ሺህ 400 ብር እየሸጡ መሆናቸውን አስታውቀዋል።

በወረዳው አጋም ውሃ ቀበሌ ነዋሪ አርሶ አደር ይማም ሰይድ በበኩላቸው ዘንድሮ በ3 ሄክታር ማሳቸው ላይ ካለሙት ሰሊጥ 13 ኩንታል ምርት ማግኘታቸውን ተናግረዋል።

በሰብል ስብሰባው 12 የጉልበት ሰራተኞችን በመጠቀም ከብክነት በፀዳ መንገድ መሰብሰብ መቻላቸውን ጠቁመው  በወቅቱ ባለው ገበያም ተጠቃሚ መሆናቸውን ገልጸዋል።

በዞኑ በመኽር ወቅቱ ከ449 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት በተለያዩ ሰብሎች የተሸፈነ ሲሆን 6 ነጥብ 4 ሚሊዮን ኩንታል ምርት እንደሚጠበቅ ዞን  ግብርና መምሪያ አስታውቋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም