ለአየር ንብረት ለውጥ ተጽዕኖ ትልቁን ድርሻ የሚይዙ ሃገራት ጠቃሚ ፖሊሲ በማውጣት ለመፍትሄው ሊሰሩ ይገባል-አምባሳደር ሮላንድ ኮቢያ

135

አዲስ አበባ (ኢዜአ) ህዳር 2/2015/ለዓለም አየር ንብረት ለውጥ መቃወስ ትልቁን የበካይነት ድርሻ የሚይዙት አገራት ቀውሱን ለመግታት ሁነኛ ፖሊሲ አውጥተው ሊሰሩ እንደሚገባ የአውሮፓ ሕብረት ልዑክ የኢትዮጵያ ፅህፈት ቤት ዋና ተወካይ አምባሳደር ሮላንድ ኮቢያ ተናገሩ።

በግብጿ ሻርማ ኤል ሸይክ ከተማ እየተካሄደ ያለው የተባበሩት መንግስታት የአየር ንብረት ለውጥ 27ኛው ‘የባለድርሻዎች ጉባዔ’ ወይም ‘ኮፕ-27’ በተለያዩ የአየር ንብረት ለውጥ አጀንዳዎች ላይ እየመከረ ነው።

የአውሮፓ ሕብረት ልዑክ የኢትዮጵያ ፅህፈት ቤት ዋና ተወካይ አምባሳደር ሮላንድ ኮቢያ ለኢዜአ እንዳሉት፤ የአየር ንብረት ለውጥ በሰው ልጅ ሕልውና ላይ ፈተና ደቅኗል።

ቀውሱ በተለይም በቀጣይ ትውልድ ላይ የሚያሳርፈውን ችግር ለመግታት መንግስታት ብርቱ ስራ ይጠብቃቸዋል ይላሉ።

ኢኮኖሚያቸው በግብርናው ክፍለ ኢኮኖሚ ላይ የተንጠለጠሉ የአፍሪካ አገራት በድርቅ፤ በጎርፍ፣ በአንምበጣ ና በሌሎችም ተፈጥሯዊ ችግሮች ክፉኛ እየተፈተኑ መሆኑን ደግሞ ለአብነት እንስተዋል፡፡

የዓለም መንግስታት በአየር ንብረት ለውጥ ላይ መክረው ስምምነት ላይ ለመድረስ የወቅቱን የአየር ንብረት ለውጥ ጉባዔ አይነት መድረኮች እንደሚያስፈልጉም ገልጸዋል።

አውሮፓ ሕብረት እና አባል አገራቱ ለጉዳዩ ልዩ ትኩረት እንደሚሰጡ ገልጸው፤ በአየር ንብረት ለውጥ ሳቢያ ለሚከሰቱ ችግሮች ዓለም በጉዳዩ ላይ በጋራ መስራት እንዳለባት አስገዳጅ መሆኑን ያሳያሉ ነው ያሉት፡፡

ለዓለም አየር ንብረት ለውጥ መቃወስ ትልቁን የበካይነት ድርሻ የሚይዙት በኤስያም ሆነ የምዕራቡ ዓለም አገራት ችግሩን ለመቀልበስ ሁነኛ ፖሊሲ ማውጣትና በቁርጠኝነት መተግባር አለባቸው ብለዋል።

በተለይም ቀውሱን መቋቋም በማይችሉ አገራት ላይ ችግሩ እንደበረታ ጠቅሰው፤ ዓለምን ከአየር ንብረት ቀውስ ለመታደግ በተለይ ያደጉ አገራት ጉዳዩ ላይ ትኩረት ሰጥተው ሊሰሩበት ይገባል ነው ያሉት።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም