ቋሚ ኮሚቴው በጦርነቱ ምክንያት የወደሙ ተቋማትን የመልሶ ግንባታ ሂደት ተዘዋውሮ ተመለከተ

133

ህዳር 2 ቀን 2015(ኢዜአ) በኢፌዴሪ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የጤና፣ ማህራዊ ልማት፣ ባህልና ስፖርት ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ በወልዲያ እና ደሴ ከተሞች በጦርነት ጉዳት የደረሰባቸው የተለያዩ አገልግሎት ሰጪ ተቋማትን ስራ ለማስጀመር እየተደረገ ያለውን የመልሶ ግንባታ ሂደት ተዘዋውሮ ተመልክቷል።

የሼህ ሙሐመድ ሁሴን አላሙዲን ስታዲየም፣ ወልዲያ ጠቅላላ ሆስፒታል፣ ወልዲያ ጤና ጣቢያ፣ ደሴ አጠቃላይ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል እና ቦሩ ሜዳ አጠቃላይ ሆስፒታል የታዩ ሲሆን በአጠቃላይ የተቋማቱ የመልሶ ግንባታና ልማት ሂደት እንዲሁም በአገልግሎት አሰጣጥ ያሉበት ደረጃ ተጎብኝቷል።

የመስክ ምልከታ ቡድኑ አስተባባሪ አቶ አበባው ደሳለኝ በጦርነቱ ማግስት የተቋማቱን የጉዳት መጠን ቋሚ ኮሚቴው በስፍራው በመገኘት መጎብኘቱን አንስተዋል።

ከወልዲያ ጤና ጣቢያ እና ከወልዲያ አጠቃላይ ሆስፒታል ውጭ በስታዲየሙ ላይ የደረሰው ጉዳት ከፍተኛ ቢሆንም ምንም አይነት የመልሶ ግንባታ ስራዎች አለመጀመራቸውን ጠቅሰው በዚህ የመልሶ ማቋቋም ሂደት ሁሉም ኢትዮጵያዊ እና ባለድርሻ አካላት ተሳታፊ እንዲሆኑ ጥሪያቸውን አቅርበዋል።

የቋሚ ኮሚቴው አባላት በበኩላቸው በአማራ ክልል ዞኖች ውስጥ የጥቃት ሰለባ የሆኑ ሴቶችና ሕጻናት እንዲሁም አረጋውያንን በጊዜያዊነት እና በዘላቂነት ለማቋቋም የሚረዱ ማኅበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ድጋፎች ተጠናክረው መቀጠል አለባቸው ብለዋል።

ጥቃት ለደረሰባቸው አካላት ማገገሚያነት የሚውሉ የአንድ ማዕከል አገልግሎት እና ሴፍ ሃውስ (safe house) በጤና ተቋማት ውስጥ ለማስጀመር እየተደረገ ያለው ርብርብ አበረታች ነው ሲሉ ተናግረዋል።

የተቋማቱ የስራ ኃላፊዎች በበኩላቸው ባለፈው ጦርነት የሰሜን ወሎ ዞን ከፍተኛ ውድመትና ዘረፋ እንደደረሰበት አንስተው፤ ከወደሙ ተቋማት በተጨማሪም በሴቶችና አረጋዊያን እንዲሁም በህብረተሰቡ ላይ ከፍተኛ የሆነ የስነ-ልቦና ጫና እና የኢኮኖሚ ችግር የደረሰ መሆኑን ገልጸዋል።

ይህን ችግር በመቋቋም አመራሩና ሕብረተሰቡ በመቀናጀት የወደሙ አገልግሎት ሰጪ ተቋማትን መልሶ ስራ ማስጀመር ተችሏል ብለዋል።

በጦርነቱ የወደሙ መሰረተ ልማቶችን መልሶ ስራ ለማስጀመር እየተደረገ ያለው ርብርብ ተጠናክሮ ሊቀጥል ይገባል ብለዋል።

መንግስት በቀጣይነትም የተጎዱ ከተሞችን ከከተሞች እና ከተቋማት ጋር ማስተሳሰር እንዲሁም ለረጂ ድርጅቶች ምቹ መደላድሎችን መዘርጋት እንዳአለበት አሰረድተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም