በዲላ ዙሪያ ወረዳ የቡና ምርታማነት በሄክታር ከሶስት እጥፍ በላይ ማሳደግ ተቻለ

132

ዲላ (ኢዜአ) ህዳር 2 ቀን 2015 በጌዴኦ ዞን ዲላ ዙሪያ ወረዳ አርሶ አደሮች ተደራጅተው ቡናን በኩታ ገጠም በማልማት ምርታማነቱ በሄክታር አምስት ኩንታል የነበረውን ከሶስት እጥፍ በላይ ማሳደግ መቻሉ ተገለጸ።

በወረዳው በጎላና ዳማ አካባቢ በኩታ ገጠም የለማ የቡና ማሳ የመስክ ምልከታ ተካሂዷል።

በመረሃ ግብሩ ላይ የጌዴኦ ዞን ግብርና መምሪያ ሃላፊ ዶክተር ዝናቡ ወልዴ ባለፈው ዓመት አንድ ሚሊዮን የሚጠጋ ያረጀ ቡና በመንቀል በተሻሻሉ ዝርያዎች መተካት መቻሉን ተናግረዋል።

እንዲሁም ቡናን ከሌላ ሰብል ጋር በስብጥር በማልማት ምርታማነትን ለማሳደግ እየተካሄደ ባለው እንቅስቃሴ ከ300 ሄክታር በላይ መሬት በኩታ ገጠም መልማቱን አመልክተዋል።

ይህም ከነባሩ ቡና አንጻር ምርታማነትን 70 በመቶ እንደሚያሳድግ ጠቁመው ዘንድሮ ከ22 ሚሊዮን በላይ የተሻሻሉ ዝሪያዎችን ለመትከል ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን ጠቅሰዋል።

ቡናን በኩታ ገጠም በስብጥር በማልማት የተገኝውን ውጤት በዞኑ ሁሉም አካባቢዎች ለማስፋት እየተሰራ ነው ብለዋል።

በወረዳው አርሶ አደሩ ቡናን ማልማት የረጅም ጊዜ ልምድ ያለው ቢሆንም በምርታማነትና ጥራት ችግር የልፋቱን ያህል ሳያገኝ መቆየቱን የተናገሩት ደግሞ የዲላ ዙሪያ ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ተገኝ ታደሰ ናቸው።

ይህንን ለመለወጥ ባለፉት ሁለት ዓመታት በተደረገ ጥረት ከ100 በላይ ሞዴል አርሶ አደሮችን በማደራጀት ከ200 ሄክታር በላይ መሬት በኩታ ገጠም ቡናን በስብጥር መልማቱን አስረድተዋል።

በዚህም በወረዳው በሄክታር ከአምስት ኩንታል ያነሰ ዝቅተኛ የቡና ምርታማነት በኩታ ገጠም በተደራጁ አርሶ አደሮች ማሳ ወደ 17 ኩንታል በማድረስ ምርታማነቱን ከሶስት እጥፍ በላይ ማሳደግ መቻሉን ገልጸዋል።

በወንዶ ገነት የግብርና ምርምር ማዕከል የአዋዳ መለስተኛ ማዕከል የቡና ተመራማሪ ለታ አጀማ ማዕከሉ ከባለድርሻ አካላት ጋር በመቀናጀትም በምርምር የተሻሻሉ ዝሪያዎችን ከመልቀቅ ባለፈ ችግኝ የማባዛትና የተሻሻሉ አሰራሮችን የማመቻቸት ስራ እያካሄደ መሆኑን ገልጸዋል።

በዚህም በዲላ ዙሪያ ወረዳን ጨምሮ በተለያዩ አካባቢዎች በቡና ምርትና ጥራት ተጨባጭ ለውጥ መምጣቱን ተናግረዋል።

አርሶ አደር ዳዊት ጅክሶ ባለፈው ለዓመት በዙሪያቸው ካሉ ሰባት አርሶ አደሮች ጋር በመቀናጀት በአምስት ሄክታር ማሳቸው ላይ ያለውን ያረጀ ቡና ተክል በመንቀል በተሻሻሉ ዝርያዎች ተክተው አሁን ላይ በጥሩ ደረጃ ላይ እንደሚገኝ ገልጸዋል።

ቡናቸው የመጀመሪያ ምርት እስኪሰጥም ሙዝ፣ እንሰትና ቦሎቄ በስብጥር በማልማት ተጠቃሚ መሆናቸውን ነው ያስታወቁት።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም