በአማራ ክልል በሩዝ ሰብል ከለማው መሬት ከ3 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ምርት እንደሚሰበሰብ ይጠበቃል--ግብርና ቢሮ

99

ባህር ዳር (ኢዜአ) ህዳር 1/2015---በአማራ ክልል በመኸር እርሻ በሩዝ ሰብል ከለማው መሬት ከ3 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ምርት ይሰበሰባል ተብሎ እንደሚጠበቅ የክልሉ ግብርና ቢሮ አስታወቀ።

በክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ዶክተር ይልቃል ከፋለ የተመራ የክልሉ ከፍተኛ የሥራ ሃላፊዎች ቡድን በደቡብ ጎንደር ዞን ፎገራ ወረዳ በኩታ ገጠም የለማን የሩዝ ሰብል ዛሬ ገብኝቷል።

በጉብኝቱ ላይ የክልሉ ግብርና ቢሮ ምክትል ሃላፊ ዶክተር አልማዝ ጊዜው እንዳሉት፣ በመኸር እርሻ ከ61ሺህ ሄክታር በላይ መሬት በሩዝ ሰብል ለምቷል።

በደቡብ ጎንደር ዞን ሩዝ አብቃይ በሆኑ ወረዳዎች ብቻ 42ሺህ ሄክታር መሬት በሩዝ ሰብል የተሸፈነ መሆኑን ገልጸዋል።

በክልሉ የሩዝ ምርታማነትን ለማሳደግ በተሰራው ሥራ አሁን ላይ በሄክታር 49 ኩንታል ማምረት እንደተቻለም ዶክተር አልማዝ አስረድተዋል።

እንደእሳቸው ገለጻ በተለይ በፎገራ ወረዳና አካባቢው ለሚገኙ አርሶ አደሮች ሩዝ ዋነኛ የምግብ ሰብል ሆኖ እያገለገለ ነው።

በክልሉ በክረምቱ የመኸር እርሻ ከለማው የሩዝ ሰብልም ከ3 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ምርት ይሰበሰባል ተብሎ እንደሚጠበቅም ተናግረዋል።

የደቡብ ጎንደር ዞን ግብርና መምሪያ ሃላፊ አቶ ቻላቸው አግደው በበኩላቸው፣ በዞኑ ሩዝ አብቃይ በሆኑት ሊቦ ከምከም፣ ፎገራ እና ደራ ወረዳዎች ከ42ሺህ ሄክታር በላይ መሬት በሩዝ ሰብል መልማቱን ተናግረዋል።

በኩታ ገጠም እየለማ ካለው መሬት ከ1 ነጥብ 9 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ምርት ይሰበሰባል ተብሎ እንደሚጠበቅም አስታውቀዋል።

አርሶ አደሩ ለሩዝ ሰብል ልማት ትኩረት በማድረጉ በተሻለ ተጠቃሚ እያደረገው መሆኑንም ገልጸዋል።

በቀጣይም ምርቱን ከብክነት በጸዳ መንገድ በመሰብሰብ መሬቱን በበጋ የመስኖ ስንዴ እና በአትክልትና ፍራፍሬ ለመሸፈን ከወዲሁ እየተሰራ መሆኑንም አቶ ቻላቸው አመልክተዋል።

በአማራ ክልል በመኸር ወቅት በተለያዩ ሰብሎች ከለማው 4 ነጥብ 8 ሚሊዮን ሄክታር መሬት 143 ሚሊዮን ኩንታል ምርት ይሰበሰባል ተብሎ እንደሚጠበቅ ከክልሉ ግብርና ቢሮ የተገኘ መረጃ ያሳያል።  

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም