የፈጠራ ስራዎች ወጪ ቆጣቢና የማህበረሰቡን እንቅስቃሴ የሚያቃልሉ ለማድረግ በትኩረት እየተሰራ ነው-የትምህርት ሚኒስቴር

148

አዲስ አበባ (ኢዜአ) ህዳር 1ቀን 2015 የፈጠራ ስራዎች ወጪ ቆጣቢና የማህበረሰቡን የእለት ከእለት እንቅስቃሴ የሚያቃልሉ ለማድረግ በትኩረት እየሰራ መሆኑን ትምህርት ሚኒስቴር ገለጸ።

በአዲስ አበባ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ በአገር አቀፍ ደረጃ ለሰባተኛ ጊዜ ሲከበር የቆየው የሳይንስ ሳምንት ተጠናቋል።

መርሃ-ግብሩም የፈጠራ ስራዎች የቀረቡበት፣ ስራ ፈጣሪዎችም ልምድ ያካፈሉበት እንዲሁም ዘርፉን ለማሳደግ ከባለድርሻ አካላት ጋር ውይይት ያካሄዱበት ነበር።

በፈጠራ ስራዎቻቸው ብልጫ ያሳዩ የፈጠራ ባለሙያ ተማሪዎችና መምህራን በማጠቃለያ መርሃ-ግብሩ ላይ እውቅና እና ሽልማት ተሰጥቷቸዋል።

በትምህርት ሚኒስቴር የምርምርና የማህበረሰብ ጉዳይ መሪ ስራ አስፈጻሚ ዶክተር ሰለሞን ቢኖርብህ የሳይንስ ሳምንት የፈጠራ ዝንባሌ ያላቸውን ተማሪዎች እና ሌሎች አካላት ያበረታታል ብለዋል።

የሳይንስ ሳምንቱ የፈጠራ ስራዎች እንዲታዩ በማድረግ ዘርፉን የመደገፍ ፋላጎት ያላቸውን አካላትን ከፈጠራ ባለቤቶች ጋር በማገናኘት የመተጋገዝ እድልን እንደሚፈጥር ገልጸዋል።

መንግስትም ለሳይንስና ቴክኖሎጂ ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ መሆኑን ጠቁመው በትምህርት ስርዓቱ ውስጥ ሳይንስና ቴክኖሎጂ በስፋት ተግባራዊ የሚሆንበት ስርዓት እየተዘረጋ መምጣቱን ተናግረዋል።

ይህም የፈጠራ አቅም ያላቸው ተማሪዎች ለውድድር እንዲቀርቡ በማድረግ ድጋፍ እንዲያገኙና በዓለም አቀፍ ደረጃም አገራቸውን ወክለው የሚወዳደሩበትን እድል የሚፈጥር ነው ብለዋል።

የመርሃ ግብሩ ተሳታፊ ተማሪዎችም፤ የሳይንስ ሳምንቱ እውቅና እና ሽልማት እንዲያገኙ ከማድረጉ ባሻገር የፈጠራ ስራዎቻቸው እንዲተዋወቁና ለህዝብ እንዲደርሱ እድል ፈጥሯል ብለዋል።

ከደቡብ ክልል ወላይታ ዞን የመጡት ወንድማማቾቹ ግርማ ዮሴፍ እና ተስፋሁን ዮሴፍ የሰብል ተባይ መርጨት የሚችል ሄሊኮፕተር እና ሌሎች መኪኖችን መስራት እንደቻሉ ተናግረዋል።

ሄሊኮፕተሯ 90 ከመቶ መጠናቀቋን ገልጸው፤ በናፍጣ ወይም በኤሌክትሪክ ኃይል መንቀሳቀስ የሚችል መኪናን በማምረት ለህብረተሰቡ በቀላል ዋጋ የማድረስ ህልም እንዳላቸውም ጠቅሰዋል።

የአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪው የ12ኛ ክፍል ተማሪ ቃልዓብ አስፋው፤ ሌዚን ሴንሲ የተሰኘ የተለያዩ ዲዛይኖችን በቀላሉ መቅረጽ የሚችል ፕሪንት ማሽን መስራቱን ገልጿል።

ውሃን በራሱ መንገድ በማንቀሳቀስ ቆጣቢ በሆነ መንገድ የጓሮ አትክልቶችን ለማጠጣትና በቀላሉ በማምረት የከተማ ግብርናን ማሳደግ የሚችል የፈጠራ ስራ ማቅረቡን የሚናገረው ደግሞ ሌላኛው የአዳማ ከተማ የ12ኛ ክፍል ተማሪ ናኦል አብዱልቃድር ነው።

የስቴም ፓወር የኢትዮጵያ ወኪል ኃላፊ ዶከተር ስሜነህ ቀስቅስ፤ ድርጅቱ በሳይንስና ቴክኖሎጂ ዝንባሌ ያላቸውን ተማሪዎች በመደገፍ የተነሱበት ዓላማ እውን እንዲሆን እየሰራ እንደሚገኝ ገልጸዋል።

ለውድድር የቀረቡት የፈጠራ ስራዎች እሴት ታክሎባቸው ጥቅም ላይ እንዲውሉም አስፈላጊው እገዛና ክትትል እንደሚደረግ አረጋግጠዋል።

በሳይንስ ሳምንት ለሚሳተፉ ተማሪዎች እውቅናና ሽልማት ከማበርከት ባሻገር በተግባር የታገዘ ልምምድ የሚያደርጉባቸው ማዕከላትን በየትምህርት ቤቶች የማቋቋም ስራው ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም