ዝርያቸው እየተመናመነ የሚገኙ አገር በቀል ዕጽዋትን በመለየት የማባዛት ስራ እየተከናወነ ነው-የጉለሌ እፅዋት ማዕከል

221

አዲስ አበባ (ኢዜአ) ህዳር 1 ቀን 2015 ዝርያቸው እየተመናመነ የሚገኙ አገር በቀል ዕጽዋትን በመለየት ተፈጥሯዊ ባህሪያቸው በተጠበቀ መልኩ የማባዛት ስራ እያከናወነ መሆኑን የጉለሌ እፅዋት ማዕከል ገለጸ፡፡

ማዕከሉ እያባዛቸው የሚገኙ አገር በቀል ዕጽዋት ለምርምር ተግባር እንዲውሉ ከከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ጋር በቅንጅት እየሰራ መሆኑንም አስታውቋል፡፡

ከአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የተወጣጡ የኮሙዩኒኬሽን የሥራ ሃላፊዎች እና ሰራተኞች የጉለሌ እጽዋት ማዕከልን ጎብኝተዋል፡፡

በዚሁ ወቅት ኢዜአ ያነጋገራቸው የጉለሌ ዕፅዋት ማዕከል ምክትል ዳይሬክተር ታምራት አስናቀ ማዕከሉ ባለፉት 13 ዓመታት ለበርካታ ዕጽዋት ጥበቃ እያደረገ ይገኛል ብለዋል፡፡

በተለይም ከአራት ዓመታት ወዲህ መንግስት ለአረንጓዴ ልማት ልዩ ትኩረት ሰጥቶ ወደ ተግባር መሸጋገሩን ተከትሎ ማዕከሉ በርካታ አገር በቀል ዛፎችን በማባዛት እና በመትከል ለደን ሽፋኑ መጨመር የራሱን አስተዋጽኦ በማድረግ ላይ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

ማዕከሉ በየዓመቱ ወደ 1 ሚሊዮን የሚጠጉ ዕጽዋትን በማፍላት ለህዝቡ በነጻ ተደራሽ ማድረጉን ገልጸው፣ ለከተማዋ የአረንጓዴ አሻራ ስኬትም ድርሻውን መወጣቱን ተናግረዋል፡፡

ጉብኝቱን አስመልክተው አስተያየታቸውን የሰጡት የሜጋ ፕሮጀክቶች ግንባታ ጽህፈት ቤት የኮሙዩኒኬሽን ዳይሬክተር አዲስ አረጋይ ማዕከሉ ዝርያቸው ሊጠፉ የተቃረቡ አገር በቀል እፅዋትን ሳይንሳዊ በሆነ መንገድ እየጠበቀ መሆኑን መመልከታቸውን ገልጸዋል፡፡

በጉለሌ ዕፅዋት ማዕከል ያሉት ሃብቶች እምብዛም ያልተዋወቁ በመሆናቸው የኮሙዩኒኬሽን አካላት ከማስተዋወቅ አንጻር የበኩላቸውን ሚና መወጣት እንዳለባቸውም ጥሪ አቅርበዋል፡፡

ማዕከሉ ለመዲናዋ ተጨማሪ ውበት የሚሰጥ ንጹህ ቦታ ስለመሆኑ የገለጹት ደግሞ የአዲስ አበባ ከተማ ሰላምና ፀጥታ አስተዳደር ቢሮ የኮሙዩኒኬሽን ዳይሬክተር ከበደ ለገሰ ናቸው፡፡

የጉለሌ ዕፅዋት ማዕከል በ705 ሄክታር መሬት ላይ ያረፈ እና በውስጡም በርካታ አገር በቀል እጽዋትን የያዘ መሆኑም ተገልጿል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም