በማስተር ፕላኑ ኢትዮጵያን ከቀጣናው የልማት ኮሪደሮች የማስተሳሰር ስራዎች በስፋት ለማከናወን ታቅዷል -የትራንስፖርት እና ሎጅስቲክስ ሚኒስትር

89

አዲስ አበባ (ኢዜአ) ሕዳር 1/2015 በብሔራዊ የትራንስፖርት እና ሎጅስቲክስ ማስተር ፕላን ኢትዮጵያን ከቀጣናው የልማት ኮሪደሮች የማስተሳሰር ስራዎች በስፋት ለማከናወን መታሰቡን የትራንስፖርት እና ሎጅስቲክስ ሚኒስትር አስታወቀ።

ሚኒስቴሩ ለቀጣይ 30 ዓመታት የሚተገብረውን ማስተር ፕላን ዛሬ ይፋ አድርጓል።

የትራንስፖርት እና ሎጅስቲክስ ሚኒስትሯ ወይዘሮ ዳግማዊት ሞገስ ማስተር ፕላኑን ተግባራዊ በማድረግ ቀጣናዊ ትስስሩን ወደ ላቀ ደረጃ ለማሻገር እንደሚሰራ ተናግረዋል።

በአሁኑ ወቅት ኢትዮጵያን የአፍሪካ የብልጽግና ተምሳሌት ለማድረግም ሁሉን አቀፍ እንቅስቃሴ እየተደረገ ይገኛል ብለዋል።


የትራንስፖርት ዘርፉን በማዘመን ኢትዮጵያን የቀጣናው ዋነኛ የሎጅስቲክስ መዳረሻ ለማድረግም  እየተሰራ መሆኑን በመግለጽ።

ማስተር ፕላኑ የኢትዮጵያን የትራንስፖርት ስርዓት ምቹ፣ቀልጣፋ፣ ከአደጋ የጸዳ፣ ደህንነቱ የተጠበቀ፣ በዘመናዊ ቴክኖሎጂ የተደገፈ፣ አስተማማኝና ተደራሽ የማድረግ ዓላማ  የያዘ መሆኑን አመልክተዋል።

የትራንስፖርትና ሎጅስቲክስ ዘርፉ የግዙፍ መሰረተ ልማቶች ዝርጋታ፣ የአገልግሎት ጥራትን የሚያረጋግጡ  ማሻሻያዎች ትግበራ፣ የሰው ኃይልና የቴክኖሎጂ አቅም ግንባታና ሌሎችን ያካትታል።

ይህንንም ለማሳካት የ30 ዓመት የተቀናጀ የትራንስፖርት ማስተር ፕላን ተግባራዊ ለማድረግ ወደ ስራ መገባቱን ነው ሚኒስትሯ ያብራሩት።

ሰነዱ ከዓለም አቀፍ ልምድ አንጻር ያሉ መልካም ተሞክሮዎች ከነባራዊ ሁኔታ ጋር እንዲናበቡ የተደረገ  ሲሆን ዘርፉ ከሌሎች የኢኮኖሚ መስኮች ጋር ያለው መስተጋብር ታሳቢ ተደርጎ ተዘጓጅቷል ብለዋል።

የትራንስፖርት እና ሎጅስቲክስ ሚኒስትር ዴኤታ ዳንጌ ቦሩ በበኩላቸው በማስተር ፕላኑ የረዥም ጊዜ ግቦች ኢትዮጵያን ከተለያዩ የልማት ኮሪደሮች ጋር በማገናኘት ሰፊ ስራዎች ለማከናወን መታሰቡን አመልክተዋል።

የማስተር ፕላኑ ዝግጅት ሁሉንም የዘርፉን ባለድርሻ አካላትና የልማት አጋሮች የተሳተፉበት አንደሆነም ጠቁመዋል።

ብሔራዊ የትራንስፖርት እና ሎጅስቲክስ ማስተር ፕላኑ ከእ.አ.አ 2022 እስከ 2052 ተግባራዊ የሚሆን ነው ተብሏል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም