ኢትዮጵያ በዓለም አቀፉ ሲቪል አቬየሽን ድርጅት ያገኘችውን የካውንስል አባልነት በዘርፉ አገራዊ ጥቅምን ለማስጠበቅ ይረዳል

204

አዲስ አበባ (ኢዜአ)  ህዳር 1ቀን 2015 ኢትዮጵያ በዓለም አቀፉ ሲቪል አቬየሽን ድርጅት ያገኝችው የካውንስል አባልነት በዘርፉ አገራዊ ጥቅምን የሚያስጠብቁ ተግባራት ላይ በትኩረት ለመስራት እንደሚያግዝ የትራንስፖርትና ሎጅስቲክስ ሚኒስትሯ ዳግማዊት ሞገስ ገለጹ።

ኢትዮጵያ በዓለም አቀፍ ደረጃ በሲቪል አቬየሽን ሁለንተናዊ ደኅንነት ቁጥጥር ላስመዘገበችው ውጤትና የክብር ተሸላሚነት አስተዋጽኦ ላበረከቱ መንግሥታዊ ተቋማት፣ ግለሰቦችና ባለድርሻ አካላት ዕውቅና ተሠጥቷል።

የትራንስፖርትና ሎጅስቲክስ ሚኒስትሯ ዳግማዊት ሞገስ፤ በዚህ ወቅት ኢትዮጵያ በአቬየሽን ዘርፉ እያስመዘገበች ያለችው ስኬትና እውቅና ዘርፉን ይበልጥ ለማሳደግ ምቹ ሁኔታን የሚፈጥር ነው ብለዋል።

ኢትዮጵያ ከ190 በላይ አባል ሀገራት ባሉት አለም አቀፉ ሲቪል አቬየሽን ድርጅት ውስጥ የካውንስል አባል እንድትሆን ሰፊ ስራ በመሰራቱ ከፍተኛ ውጤት ለማስገኘት አስችሏል።

ኢትዮጵያ በአለም አቀፉ ሲቪል አቬየሽን የካውንስል አባል ሆና መመረጧ በዘርፉ በአለም አቀፍ ደረጃ ሀገራዊ ተጠቃሚነትን የሚያረጋግጡ ውሳኔዎችን ለማሳላፍ እድል የሚሰጥ መሆኑንም እንዲሁ።

በቀጣይም በዘርፉ የኢትዮጵያን ብሔራዊ ጥቅም የሚያስጠብቁ  ተግባራት እንዲከናወኑ በትኩረት ይሰራል ነው ያሉት።

በአሁኑ ወቅት የኢትዮጵያ አየር መንገድ መዳረሻና አገልግሎት እያደገ መምጣቱን ተከትሎ የአቬየሽን ቁጥጥርና ደኅንነትን የሚያሳድጉ ስራዎች ትኩረት የሚያስፈልጋቸው ጉዳዮች ናቸው ብለዋል።

ለዚሁ ስኬትም የትራንስፖርት ዘርፉ የ10 ዓመቱ መሪ እቅድ የአቬየሽን ዘርፉን አቅም የሚያሳድጉ ግቦች መቀመጣቸውን ነው የተናገሩት።

የኢትዮጵያ የሲቪል አቬየሽን ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ጌታቸው መንግሥቴ፤ በበኩላቸው ኢትዮጵያ በአቪየሽን ዘርፍ ቀደምት ታሪክ ያላት ሃገር ናት ብለዋል።

በአሁኑ ወቅት በአለም አቀፍ ደረጃ በሲቪል አቬየሽን ሁለንተናዊ ደህንነት ቁጥጥር መስክ የተመዘገበው ውጤት የኢትዮጵያ የአየር ትራንፖርት አገልግሎት አስተማማኝነትን የሚያረጋግጥ እንደሆነም ተናግረዋል።

በተጨማሪም የኢትዮጵያ አየር መንገድ በዓለም አቀፍ መዳረሻዎቹ ያለው ተቀባይነትም እንዲጨምር ያደርጋልም ነው ያሉት።

በቀጣይም ኢትዮጵያ በዘርፉ ያላትን እምቅ አቅም በመጠቀም የአቬየሽን ኢንዱስትሪውን ለማሳደግ ከግሉ ዘርፍ ጋር ሰፊ ስራዎች እንደሚሰሩም አመልክተዋል።

ከዚህ ውስጥም የአውሮፕላን ጥገናና እድሳት ተጠቃሽ መሆናቸውን ነው ያመለከቱት።

ኢትዮጵያ በ41ኛው የዓለም አቀፉ የሲቪል አቬየሽን ድርጅት ካውንስል አባል ሆና ለሚቀጥሉት 3 ዓመታት እንድታገለግል ድምጽ ከሰጡ 175 ሀገራት መካከል የ154 ቱን ድምጽ በማግኘት መመረጧ ይታወሳል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም