የልማትና የመልካም አስተዳደር ችግሮችን ለመፍታት ህወሃት የሚያደርገው ጥረት እንደግፋለን..እህት ድርጅቶች

66
መስከረም 16/2011 ህወሃት ልማትን ለማስቀጠልና የመልካም አስተዳደር ችግሮችን ለመፍታት ለሚያደርገው ጥረት በጋራ  እንደሚሰሩ  እህት ድርጅቶች ተናገሩ  ፡፡ በ13ኛው የህወሃት ድርጅታዊ ጉባኤ ላይ በክብር እንድግድነት የተሳተፉ እህት ድርጅቶች  የድጋፍ  መልእክት አስተላልፈዋል፡፡ በጉባኤው ላይ መልእክት ያስተላለፉት የብአዴን ተወካይ እንዳሉት የትግራይና የአማራ ህዝብ በፍቅር አብሮ በመኖር አምባገነን ስርአትን ለማስወገድ  የአማራ ወጣቶች ባደረጉት ትግል የትግራይ ህዝብ  ድጋፍ ከፍተኛ ነው፡፡ አንድነትን በማጠናከር የምሰራበት ግዜ  በመሆኑ ድርጅታቸው ከህወሃት ጋር እንደሚሰራም ገልጸዋል፡፡ የደኢህዴን ተወካይ በበኩላቸው የትግራይ ህዝብ በአጼዎቹና በአንባገነኑ ስርአት የነበረን  የመብት ጥሰት ለማስወገድ የከፈለው መስዋዕትነት በሀገሪቱ ዴሞክራሲን ለመተግበር የማይተካ ድርሻ አበርክቷል ብለዋል፡፡ ድርጅቱም ህዝብን በማታገል ባለው የረጅም አመት ልምድ  የዜጎችን የመልካም አስተዳደርና የልማት ጥያቄ ለመመለስ ላበረከተው አስተዋጽኦ ደኢህዴን ምስጋና እንደሚያቀርብ ተናግረዋል፡፡ ህወሃት ልማትን ለማረጋገጥና የመልካም አስተዳደር ችሮችን ለመፍታት ለሚቀይሳቸው መንገዶች በጋራ እንደሚሰሩም ገልጸዋል፡፡ በሀገሪቱም ሆነ በክልላቸው ለተመዘገቡ የልማትና የዴሞክራሲ  ውጤቶች የህወሃት የረጅም አመት የትግል ልምድ ትልቅ አቅም ያአለው  እንደነበር የገለፁት  ደግሞ  የኦዴፓ ተወካይ ናቸው ፡፡ አሁን በሀገሪቱ የሚታየውን ለውጥ ማስቀጠል የሚያስችል  ውይይት ለማድረግ  ምሁራንና ወጣቶችን በለውጡ ቀጥተኛ ተሳታፊ የሚያደርጉ ውሳኔዎች በጉባኤው እንደሚያሳልፍ  እምነት አለን ብለዋል፡፡ ኦዴፓ ከእህት ድርጅቱ ህውሃት ጋር ያለውን በጋራ ተጠቃሚነት ላይ የተመሰረተ ግንኙነት ለማጠናከር እንደሚሰራም አስታውቀዋል፡፡ ኢትዮጵያ የህዝቡ የልማትና የዴሞክራሲ ጥያቄ ተመልሶ የተረጋጋችና ሰላማዊ አገር አንድትሆን ኦዴፓ የሚጠበቅበትን ማንኛውም መስዋዕትነት ለመክፈል ዝግጁ መሆኑንም  አረጋግጠዋል። በድርጅታዊ ጉባኤው ላይ 1 ሺህ 650 ሰዎች እየተሳተፉ ሲሆን የተፎካካሪ ፓርቲ ተወካዮችም ተሳታፊዎች ናቸው። በጉባኤው የ12ኛ የድርጅቱን ውሳኔዎች አፈፃፀም የሚገመግም ሲሆን  አለም አቀፋዊ፣ አገራዊና ክልላዊ ጉዳዮች ላይ ውይይት እንደሚደረግም ተገልጿል። የድርጅቱን ህገ-ደንብ ለማሻሻል በተዘጋጀ ሰነድ ላይ ተወያይቶ ውሳኔ ማሳለፍና የቀጣይ ዓመታት አቅጣጫዎችን ማስቀመጥ ከጉባኤው የሚጠበቁ ጉዳዮች ናቸው። ድርጅቱ በጉባኤው ላይ ሊቀመንበር እና ምክትል ሊቀመንበርን ጨምሮ አዳዲስ የስራ አስፈጻሚዎችና የማዕከላዊ ኮሚቴ አባላትን ይመርጣል ተብሎ ይጠበቃል።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም