በክልሉ የተጀመሩ አገልግሎት ሰጪ ፕሮጀክቶችን ለማጠናቀቅ በትኩረት እየተሰራ ነው- ዶክተር ይልቃል ከፋለ

87

ባህር ዳር ጥቅምት 30/2015(ኢዜአ) የክልሉ መንግስት ቀደም ሲል የተጀመሩ ፕሮጀክቶችን በማጠናቀቅ ለህዝብ አገልግሎት እንዲበቁ በትኩረት እየሰራ እንደሚገኝ የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳደር ዶክተር ይልቃል ከፋለ አስታወቁ።

የባህር ዳር ዓለም አቀፍ ስታዲዮም  ሁለተኛው ዙር ቀሪ ስራ ግንባታ በ1 ቢሊዮን ብር ወጭ ለማጠናቀቅ የፌደራልና የክልል አመራሮች በተገኙበት ዛሬ ተጀምሯል።

ርዕሰ መስተዳደሩ በማስጀመሪያው  መረሃ-ግብር ላይ፤  ስፖርት መዝናኛ ብቻ ሳይሆን የኢኮኖሚ ምንጭም ጭምር መሆኑን ገልጸዋል።

ስታዲዮሙ ከፍተኛ  በጀት ተመድቦለት ተጀምሮ ሳይጠናቀቅ መቆየቱ ህዝቡ  ከዘርፉ የሚያገኘውን ጥቅም ማስተጓጎሉን ተናግረው የክልሉ መንግስት ስታዲዮሙ የፊፋን መስፈርት አሟልቶ ዓለም አቀፍ ጨዋታዎችን እንዲያስተናግድ በትኩረት  እየሰራ እንደሆነም አስረድተዋል።

ቀደም ሲል የተጀመሩና ያልተጠናቀቁ ፕሮጀክቶችን ጭምር አጠናቆ ለህዝብ አገልግሎት እንዲበቁ የክልሉ መንግስት አቅጣጫ አስቀምጦ ተግባራዊ እንቅስቀሴ ላይ እንደሚገኝ  አስታውቀዋል።

የስታዲዮሙ ግንባታ በአንድ ዓመት ጊዜ ተጠናቆ ዓለም አቀፍ ጨዋታዎችን እንዲያስተናግድ  ርብርብ  እንደሚደረግ ርዕሰ መስተዳደሩ አረጋግጠዋል።

በመረሃ ግብሩ ላይ የተገኙት የባህልና ስፖርት ሚኒስትር አቶ ቀጀላ መርዳሳ በበኩላቸው፤ የባህር ዳር ዓለም አቀፍ ስታዲዮምን 2ኛ ዙር ግንባታ ለማጠናቀቅ የፌዴራል መንግስት  ድጋፍ እዲያደርግ እንደሚሰራ አስታውቀዋል።

ግንባታውን የሚያከናውነው የሜድሮክ ኢንቨስትመንት ግሩፕ ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ ጀማል አህመድ እንዳሉት፤  ግንባታው በቶሎ እንዲጠናቀቅ የሜድሮክ ኢንቨስትመንት ግሩፕ ይህ ችግር እንዲቃለል  በገንዘብ ከማገዝ ጀምሮ እየሰራ መሆኑን ተናግረዋል።

ታህሳስ 2002 ዓ.ም በ42 ሄክታር መሬት ላይ ግንባታው የተጀመረው የባህር ዳር ዓለም አቀፍ ስታዲዮም ተጨማሪ  ሁለት መለማመጃ ሜዳዎችን ጨምሮ ለኦሎምፒክ ስፖርት በሚሆን መልኩ ከ20 ስፖርት ዓይነቶች የሚበልጡ በአንድ ጊዜ ማስተናገድ እንደሚችል  ተገልጿል።

የስታዲዮሙ ሁለተኛው ዙር ቀሪ የግንባታ ስራ  የክልሉ መንግስት በመደበው 700 ሚሊዮን ብርና የሜድሮክ ኢንቨስትመንት ግሩፕ ባደረገው የ300 ሚሊዮን ብር ድጋፍ የሚከናወን እንደሆነም ተመልክቷል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም