ዩኒቨርሲቲው ለደባርቅ ከተማ የውሃ አቅርቦት ችግር ለመፍታት 19 ሚሊዮን ብር የሚገመት ድጋፍ ማድረግ ጀመረ

132

ጎንደር ፤ ጥቅምት 30 ቀን 2015(ኢዜአ) ፡- የደባርቅ ከተማን የንጹህ መጠጥ ውሃ አቅርቦት ችግር ለመፍታት የመሰረተ ልማት ዝርጋታ የሚውል 19 ሚሊዮን ብር የሚገመት የቁሳቁስ ድጋፍ ማድረጉን የደባርቅ ዩኒቨርሲቲ አስታወቀ፡፡

የዩኒቨርሲቲው ፕሬዚዳንት ዶክተር ጀጃው ደማሙ ለኢዜአ እንደተናገሩት፤ ድጋፉ ቁጥሩ እያደገ የመጣውን የከተማዋን ህዝብ የንጹህ መጠጥ ውሃ ፍላጎት ለማሟላት የሚያግዝ ነው፡፡

ተቋሙ ቀደም ሲል በ27 ሚሊዮን ብር ወጪ ጥልቅ የውሀ ጉድጓድ በማስቆፈር ለከተማው አገልግሎት እንዲውል ማዘጋጀቱን ጠቅሰዋል።

አሁን ላይ ይህን ጉድጓድ ከከተማው የውሃ መስመር በማገናኘት ለህዝብ ግልጋሎት እንዲውል የቁሳቁስ ድጋፍ ማድረግ መጀመሩን አስታውቀዋል።

በመጀመሪያ ዙርም 3 ሚሊዮን ብር የሚያወጣ 70 ከፍተኛ የውሃ ማስተላለፊያ የቱቦ መስመሮችን ዛሬ ለከተማዋ  አስተዳደር ውሃና ፍሳሽ አገልግሎት ጽህፈት ቤት ማስረከባቸውን አረጋግጠዋል፡፡

በተጨማሪም በ16 ሚሊዮን ብር ወጪ የተገዙ የውሃ ፓንፕ ፣የኤሌክትሮ መካኒክ መሳሪያዎችና የኤሌክትሪክ ጄኔሬተር በቅርቡ እንደሚያስረክቡ ገልጸዋል።

''ዩኒቨርሲቲው ለውሃ መሰረተ ልማት ግንባታ ያደረገው ድጋፍ የከተማዋን የውሃ አቅርቦት ከ20 በመቶ ወደ 35 በመቶ ለማሳደግ የሚግዝ ነው'' ያሉት ደግሞ  የከተማዋ አስተዳደር ውሃና ፍሳሽ አገልግሎት ጽህፈት ቤት ሃላፊ አቶ እንዳልክ ጠጁ ናቸው፡፡

ከፍተኛ የውሃ ማስተላለፊያ ቱቦዎቹ ዩኒቨርሲቲው በራሱ ወጪ አስቆፍሮ ለከተማው መጠጥ ውሃ አገልግሎት እንዲሆን በነጻ የሰጠውን ከዋናው መስመር ጋር ለማገናኘት ለሚዘረጋው የአንድ ነጥብ 6 ኪሎ ሜትር የመስመር ግንባታ እንደሚውል ገልጸዋል፡፡

ቁጥሩ በከፍተኛ ደረጃ እየጨመረ ከመጣው የከተማዋ ነዋሪ አንጻር የከተማው የውሃ ፍላጎትና አቅርቦት ሊመጣጠን እንዳልቻለም ሃላፊው ተናግረዋል፡፡

በአሁኑ ወቅት ለከተማው በቀን 4 ሺ 500 ሜትር ኪዩብ ውሃ  የሚያስፈልግ ቢሆንም እየቀረበ ያለው ግን ከአንድ ሺህ 200 ሜትር ኪዩብ እንደማይበልጥ ጠቅሰዋል፡፡

ጥልቅ ጉድጓዱ ወደ አገልግሎት ሲገባም የአቅርቦት መጠኑን በቀን ከ1 ሺህ 600 ሜትር ኪዩብ በላይ ለማሳደግ ያስችላል ብለዋል።

የከተማው ውና ፍሳሽ አገልግሎት ጽህፈት ቤት 6ሺህ 800 የውሃ ደንበኞች ሲኖሩት በከተማው ከ90 ሺህ በላይ ህዝብ እንደሚኖር ከሃላፊው ገለጻ ለመረዳት ተችሏል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም