በአማራ ክልል የባዮ ጋዝ ኢነርጂን በማስፋፋት የገጠሩን ማህበረሰብ ተጠቃሚነት ለማሳደግ እየተሰራ ነው-ቢሮው

160

ባህር ዳር ጥቅምት 30/2015(ኢዜአ) በአማራ ክልል የባዮ ጋዝ ኢነርጂ ግንባታን በማስፋፋት የገጠሩን ህብረተሰብ የኑሮ ሁኔታ ለመለወጥ እየተሰራ መሆኑን የክልሉ ውሃ እና ኢነርጂ ቢሮ አስታወቀ።

በባዮ ጋዝ ግንባታ የላቀ አፈጻጸም ላስመዘገቡ ተቋማትና ግለሰቦች እውቅናና ሽልማት የተሰጠበት የኢነርጂ ፌስቲቫል በሰሜን ሜጫ ወረዳ ቁርጥ ባህር ቀበሌ ትናንት ተካሂዷል።

የአማራ ክልል ውሃና ኢነርጂ ቢሮ ሃላፊ ዶክተር ማማሩ አያሌው በእዚህ ወቅት እንዳሉት የብሔራዊ የባዮ ጋዝ ልማት መርሃ ግብርን ወደ ሥራ በማስገባት ጉልበት፣ ጊዜና ወጪን በመቆጠብ የአየር ንብረት ሚዛንን ለመጠበቅ እየተሰራ ነው።

የባዮ ጋዝ ስራ ማዳበሪያን በመተካት ለግብርና ምርታማነት እድገት አስተዋጽኦ የጎላ በመሆኑ በአርሶ አደሩ ዘንድ ተቀባይነቱ እያደገ መጥቷል ብለዋል።

ከሁለት ዓመት በፊት በተጀመረው የ10 ዓመት ስትራቴጂክ ዕቅድም ከ35 ሺህ በላይ የባዮ ጋዝ ማብላያ በመገንባት የህብረተሰቡን የታዳሽ ሃይል ተጠቃሚነት ለማሳደግ እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።

ዶክተር ማማሩ እንዳሉት ባለፈው ዓመት 1ሺህ 471 የባዮ ጋዝ ማብላያ ግንባታ በክልሉ ለማካሄድ ታቅዶ 2 ሺህ 341 የባዮ ጋዝ ማብላያ መገንባት ተችሏል።

በምዕራብ ጎጃም ዞን 3ሺህ 359 የባዮ ጋዝ ማብላያዎች ተገንብተው ለአርሶ አደሩ አገልግሎት እየሰጡ መሆኑን የገለጹት ደግሞ የዞኑ ዋና አስተዳዳሪ አቶ መልካሙ ተሾመ ናቸው።

ከተገነባው የባዮ ጋዝ ተረፈ ምርት 12 ሺህ 477 ሜትር ኪዩብ የተፈጥሮ ማዳበሪያ በማምረት ለግብርና ልማት ሥራ በመዋሉ የሰብል ምርታማነትን ለማሳደግ መቻሉን ጠቁመዋል።

የአማራ ክልል ብልጽግና ፓርቲ ጽህፈት ቤት ተወካይ ዶክተር ዘሪሁን ፍቅሩ በበኩላቸው፣ "በክልሉ በአጠቃላይ 77 ሺህ 800 አርሶ አደሮች ባዮ ጋዝ ግንባታ በማካሄድ ከመብራት እና ከምግብ ማብሰያነት ባለፈ ለማዳበሪያ በመጠቀም ኑሯቸውን እያሻሻሉ ነው።

"ባዮጋዝ ገንብተን መጠቀማችን በተለይ በሴቶች ላይ ይደርስ የነበረውን ጫና ቀንሶልናል" ያሉት ደግሞ በሰሜን ሜጫ ቁርጥ ባህር ቀበሌ ናዋሪ ወይዘሮ ብርሃኔ ደሳለኝ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም