አለም አቀፉ ማህበረሰብ ለሰላም ስምምነቱ ስኬት አስፈላጊውን ድጋፍ ለማድረግ አጋርነቱን እያሳየ ነው- የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር

123

አዲስ አበባ (ኢዜአ) ጥቅምት 30 ቀን 2015 አለም አቀፉ ማህበረሰብ ለሰላም ስምምነቱ ስኬት አስፈላጊውን ድጋፍ ለማድረግ አጋርነቱን እያሳየ መሆኑን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ገለጸ።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል-አቀባይ አምባሳደር መለሰ አለም ሳምንታዊ መግለጫ ሰጥተዋል።

ቃል-አቀባዩ በመግለጫቸው በአለም አቀፍ ግንኙነትና ዲፕሎማሲ በሳምንቱ የተሰሩ አንኳር ጉዳዮችን ዳስሰዋል።

አለም አቀፉ ማህበረሰብ በመንግስትና ህወሓት መካከል የተፈረመው የሰላም ስምምነት ተግባራዊ ለማድረግ በሚደረገው እንቅስቃሴ አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርግ እየገለጸ መሆኑን ተናግረዋል።

በዚህም የተለያዩ ሀገራት፣ የአለም አቀፍ፣ አህጉራዊ፣ እና ክፍለ አህጉራዊ ድርጅቶች፣ አለም አቀፍ  የፋይናንስ ተቋማት መንግስትና ህወሓት የደረሱበትን ስምምነት በአዎንታ እንደሚቀበሉና አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚሰጡ መልዕክቶችን ማስተላለፋቸውን አስታውቀዋል።

በጦርነቱ ጉዳት የደረሰባቸው አካባቢዎችን መልሶ ለማቋቋም በሚደረገው ጥረት ድጋፍ እንደሚያደርጉ መግለጻቸውን ቃል አቀባዩ ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም