በተለያዩ ምክንያቶች ግንባታቸው ተቋርጦ የነበሩ ሁለት የመንገድ ፕሮጀክቶችን በተያዘው በጀት ዓመት በማጠናቀቅ ለትራፊክ ክፍት ይደረጋሉ

175

አዲስ አበባ (ኢዜአ) ጥቅምት 30 ቀን 2015 በአዲስ አበባ ከተማ በተለያዩ ምክንያቶች ግንባታቸው ተቋርጦ የነበሩ ሁለት የመንገድ ፕሮጀክቶችን በተያዘው በጀት ዓመት በማጠናቀቅ ለትራፊክ ክፍት እንደሚደረጉ ተገለጸ።

የመንገዶቹ ግንባታ ዳግም መጀመሩን የከተማዋ ኮሙዩኒኬሽን ቢሮ አስታውቋል።

ለመንገዶቹ ግንባታ መቋረጥ የወሰን ማስከበርና ከገንዘብ ጋር የተያያዙ ችግሮች መሆናቸውም ተመላክቷል።

ግንባታቸው ተቋርጦ የነበሩት መንገዶች የቃሊቲ-ቱሉ ዲምቱ አደባባይ እና ከቃሊቲ ቀለበት መንገድ አደባባይ - ቡልቡላ - ቂሊንጦ አደባባይ ያሉ ፕሮጀክቶች እንደሆኑም ተገልጿል።

የቃሊቲ -ቱሉ ዲምቱ የመንገድ ፕሮጀክት የቀኙ መስመር የመጀመሪያ ደረጃ የአስፋልት ንጣፍ ስራ እና የሦስት ማሳለጫ ድልድዮች የስትራክቸር ስራ ተከናውኖ መንገዱ በከፊል ለትራፊክ ክፍት መሆኑን አስታውሷል፡፡

ግንባታውን ዳግም ለመጀመር ከፋይናንስ ጋር በተያያዘ አጋጥሞ የነበረው ችግር ከፌዴራል መንግስት በተገኘ ድጋፍ የመንገዱ ግንባታ በመከናወን ላይ እንደሚገኝ አስታውቋል፡፡

ፕሮጀክቱ እስከ ሰኔ 30 ቀን 2015 ዓ.ም ድረስ የመጀመሪያ ደረጃ አስፋልት በማልበስ ለትራፊክ ክፍት ለማድረግ እየተሰራ ይገኛል፡፡

ይህ የመንገድ ፕሮጀክት በቻይና ኮሚኒኬሽን ኮንስትራክሽን ካምፓኒ እየተከናወነ የሚገኝ ሲሆን 11 ኪ.ሜ ርዝመትና 50 ሜትር የጎን ስፋት እንዳለውም ቢሮው ጠቁሟል፡፡

በተመሳሳይ የቃሊቲ ቀለበት መንገድ አደባባይ-ቡልቡላ-ቂሊንጦ አደባባይ ፕሮጀክት 10 ነጥብ 5 ኪሎ ሜትር ርዝመት ያለው ሲሆን ከዚህ ውስጥ 5 ነጥብ 6 ኪሎ ሜትር የሚሆነው አስፋልት መልበሱን ተገልጿል።

በአሁኑ ወቅት የድልድይ ስራ እየተከናወነለት ሲሆን በዚህ በጀት ዓመት ቀሪ የግንባታ ስራዎችን በማጠናቀቅ መንገዱን ለትራፊክ ክፍት ለማድረግ እየተሰራ እንደሚገኝ ነው የተጠቀሰው፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም