ደኢሕዴን በክልሉ ለሚስተዋሉ ወቅታዊ ችግሮች ዘለቄታዊ መፍትሄ ማስቀመጥ አለበት- ምሁራን

113
ሚዛን መስከረም 15/2011 የደቡብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ /ደኢሕዴን/ድርጅታዊ ጉባዔ በክልሉ ለሚስተዋሉ ወቅታዊ ችግሮች ዘለቄታዊ መፍትሄ ማስቀመጥን ቀዳሚ አጀንዳው ማድረግ  እንደሚገባው ምሁራን አሳሰቡ፡፡ ከመስከረም 18 እስከ 21/2010 የሚካሄደውን ንቅናቄ አስመልክቶ ኢዜአ ከሚዛን ቴፒ ዩኒቨርሲቲ ምሁራን ጋር ቃለ ምልልስ አድርጓል ፡፡ ጉባዔው በክልሉ እየተስተዋሉ ያሉ ወቅታዊ ችግሮች በዘላቂነት መፍታት በሚችሉበት ሁኔታ ላይ ትኩረቱን አድርጎ ሊመክር  እንደሚገባ ምሁራኑ ገልጸዋል። በዩኒቨርሲቲው የማህበራዊ ሣይንስ ትምህርት ክፍል ኃላፊና መምህር አዲሱ ጉታ በክልሉ ፈጣን ምላሽ የሚያሻቸው ችግሮች እንደሚስተዋሉ ገልጸው፣ከነዚህም የሰላምና ጸጥታ ችግሮችን መለየትና መፍትሄ ማስቀመጥ የጉባዔው ዓብይ አጀንዳ ሊሆን ይገባል ብለዋል። ደኢህዴን  ህዝቡን የሚያደምጡ፣ ለችግሮች ፈጣን ምላሽ የሚሰጡና ህዝባዊ ተቀባይነት ያላቸው ብቁ አዳዲስ አመራሮችን ማካተት እንዳለበትም ጠቁመዋል። ነባራዊ ክልላዊ ጉዳዮችን በዘላቂነት በመፍታትም አገራዊ ለውጡን ማስቀጠል ያስፈልጋል ብለዋል፡፡ በክልሉ ለዓመታት ሳይፈቱ የቆዩና አሁንም መልስ ያላገኙ ጥያቄዎች ዘላቂ መፍትሔ ሊሰጣቸው እንደሚገባ የገለጹት ደግሞ የሕግ መምህሩ  ጌታሁን ተሾመ ናቸው። በክልሉ በሚገኙ በርካታ አካባቢዎች የመዋቅርና አደረጃጀት ጥያቄዎች እንዲሁም የልማት ፍላጎቶች በተደጋጋሚ ከህዝቡ መነሳታቸውን አስታውሰው፣ህዝቡ ለሚያቀርባቸው ጥያቄዎች ፈጣን ምላሽ መስጠት ያስፈልጋል ብለዋል። በክልሉ አንዳንድ አካባቢዎች እየተከሰቱ ያሉትን የሰላምና ጸጥታ ችግሮችን መፍታትና የህግ የበላይነትን ማረጋገጥ ቅድሚያ ሊሰጠው እንደሚገባም  መምህር ጌታሁን ገልጸዋል። በዩኒቨርሲቲው የፌደራሊዝም መምህር መለስ ቸኮል በበኩላቸው ጉባዔው አዲሱን የለውጥ ጉዞ  የሚያስቀጥል አዳዲስ አመራር ወደ መዋቅሩ ማምጣት  እንደሚገባው አሳስበዋል፡፡ ጉባዔው የክልሉን ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ፍላጎቶችን በአስተማማኝነትና በዘላቂነት ለመፍታት ትኩረት መስጠት እንዳለበትም አስገንዝበዋል፡፡ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ እየታዩ ያሉትን የአከላል ጥያቄዎችን በጥናት ላይ በመመርኮዝ ምላሽ መስጠት ያሻል፡፡ ደኢህዴን በክልሉ እየታዩ ያሉ ዘርፈ- ብዙ ችግሮች በጊዜ መፍትሔ ለመስጠት ከፌዴራል መንግሥት ጋር በመሆን አቅጣጫ ማስቀመጥ አለበት ሲሉ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል፡፡  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም