በዘንድሮው ዓመት ከ3 ሺህ ኩንታል በላይ አቮካዶ ወደ ውጭ ለመላክ እየተሰራ ነው - ቢሮው

233

አዳማ ጥቅምት 29/2015(ኢዜአ) በዘንድሮው ዓመት ከ3ሺህ ኩንታል በላይ የአቮካዶ ምርት ወደ ውጭ ለመላክ እየሰራ እንደሚገኝ የኦሮሚያ ክልል ግብርና ቢሮ ገለፀ ።

በቢሮው የቡናና ፍራፍሬ ዘርፍ ምክትል ሃላፊ አቶ ሙሐመድሳኒ አሚን ለኢዜአ እንደገለፁት የክልሉ መንግስት የግብርና ዘርፉን ለማዘመን አቮካዶን ጨምሮ በሙዝና ፓፓዬ በመሳሰሉት ልማት ላይ ኢንሼቲቭ ቀርፆ ወደ ተግባር መግባቱን አስታውሰዋል ።

በዚህም ባለፉት ሶስት ዓመታት በተለይም አቮካዶን ለውጭ ገበያ በማምረቱ ላይ ትኩረት አድርገው እየሰሩ መሆናቸውን ገልጸው፤ በእስከ አሁኑ ሂደትም አቮካዶው ብቻ በ10 ሺህ ሄክታር ላይ መተከሉን ተናግረዋል።

በመጀመሪያው ዓመት የተተከለው አቮካዶ ምርት መስጠት መጀመሩን የገለፁት አቶ ሙሐመድሳኒ፤ በዚህም  አርሶ አደሮቹ 180 ኩንታል ወደ ዓለም ገበያ በመላክ የውጭ ምንዛሪ ማስገኘት መጀመራቸውን ገልጸዋል።

ዘንድሮም  ምርቱ እየጨመረ በመሆኑ 3ሺህ ኩንታል ለመላክ ታቅዶ እየተሰራ መሆኑን የገለጹት ምክትል ሃላፊው፤ በአሁኑ ወቅት አንዱ ኪሎ ግራም ከ60 ብር በላይ እየደረሰ ላለው የአቮካዶ ምርት ዋጋ የተቆረጠለት መሆኑን አመልክተዋል ።

በዚህም አርሶ አደሩ ምርቱን ቀጥታ ወደ ውጭ መላክ እንዲችል ሁኔታዎችን የማመቻቸት ስራ እየተሰራ መሆኑን ጠቅሰው፤ ምርቱን በስፔን፣ ቻይና፣ ጣሊያን እንዲሁም ወደ መካከለኛው ምስራቅ ሀገራት ለመላክ እየሰሩ መሆናቸውን ገልጸዋል።

ከዚህም 500ሺህ የአሜሪካን ዶላር ለማግኘት መታቀዱን አክለዋል ምክትል ሃላፊው።

በዘርፉ ልማት ከተሰማሩት አርሶ አደሮች መካከል የሉሜ ወረዳ ነዋሪ አርሶ አደር  ተስፋዬ በዳዳ እንዳሉት በአሁኑ ወቅት ከ2 ሄክታር በላይ መሬት ላይ አቮካዶን ለውጭ ገበያ እያለሙ መሆኑን ጠቅሰው ይበልጥ ለማስፋፋት ማቀዳቸውንም ተናግረዋል።

ባለፈው አመት በሁለት ዙር ሽያጭ 2 ሚሊዮን ብር በላይ ገቢ ማግኘታቸውን ጠቅሰው፤ አሁንም የመሸጫ ዋጋ ወጥቶላቸው ምርቱን በጥራት እያዘጋጁ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

አቮካዶ ከገቢ ማስገኛነት ባለፈ ልጆቻችን የተመጣጠነ ምግብ እንዲያገኙ አስችሏል ያሉት ደግሞ ሌላኛው አስተያየት ሰጪ አርሶ አደር ረዲኤቱ ረጋሳ ናቸው።

ከሶስት ዓመት በፊት ሶስት አርሶ አደር ሆነው በምስራቅ ሸዋ ዞን ሉሜ ወረዳ ሸራ ዲባንዲባ ቀበሌ የጀመሩት አርሶ አደሮች ዛሬ ላይ ከ90 በላይ መድረሳቸውን አመልክተዋል።

የመንግስት ድጋፍና ክትትል በቅርብ መሆኑ ተጠቃሚ እንዲሆኑ እያስቻላቸው መሆኑንም ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም