የስንዴን ምርታማነት ለማሻሻል በምርምር የተደገፈ ስራ እያከናወነ መሆኑን የሐረማያ ዩኒቨርሲቲ አስታወቀ

179

ሐረር ፤ ጥቅምት 28 ቀን 2015(ኢዜአ) ፡- የስንዴን ምርታማነት ለማሻሻልና የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ በምርምር የተደገፈ ስራ እያከናወነ መሆኑን የሐረማያ ዩኒቨርሲቲ አስታወቀ።

ዩኒቨርሲቲው በምስራቅ ሐረርጌ ዞን  በበጋ ወራት የሚለማ 1ሺህ  ኩንታል  የስንዴ  ምርጥ ዘር ዛሬ ድጋፍ አድርጓል።

በድጋፍ አሰጣጡ ሥነ-ሥርዓት ላይ የዩኒቨርሲቲው የምርምር ጉዳዮች ምክትል ፕሬዚዳንት ዶክተር ተስፋዬ ለማ፤ ተቋሙ የአርሶ አደሩን ምርታማነትን ለማሻሻል በተፈጥሮ ሃብት አጠቃቀም፣ሰብልና በእንስሳት ልማት ዘርፎች የምርምር ስራዎችን እንደሚያከናውን ገልጸዋል።

በተለይ በኦሮሚያ ምዕራብና ምስራቅ ሐረርጌ ዞኖች እንዲሁም በሐረሪ ክልል የስንዴ ምርታማነት እንዲጨምር ዩኒቨርሲቲው ባለፉት ሁለት ዓመታት በ210 ሄክታር መሬት ላይ አርሶ አደሩን በኩታ ገጠም  በማደራጀት ስንዴን በመስኖ እንዲያባዙ ሲደግፍ መቆየቱንም ጠቅሰዋል።

በተለይ የስንዴን ምርታማነት ለማሻሻልና የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ በምርምር የተደገፈ ስራን እያከናወነ እንደሚገኝ አስታውቀዋል።

ዘንድሮ  በምስራቅ ሐረርጌ ዞን ቆላማ ወረዳዎች ውስጥ በ1ሺህ ሄክታር ላይ ምርጥ የስንዴ ዘርን ለማባዛት ድጋፍ መደረጉም ተመልክቷል።

በተጨማሪም ተቋሙ  አርሶ አደሩና የግብርና ባለሙያው  የቴክኖሎጂ ተጠቃሚ እንዲሆን የአቅም ግንባታ ስልጠና ፣የክትትልና የቴክኒክ ድጋፍ እንደሚያደርግ ጠቁመው፤በተለይ ዘንድሮ ዩኒቨርሲቲው በአፈርና በመስኖ ውሃ  አጠቃቀም ላይ የምርምር ስራዎችን እንደሚያከናውን ተናግረዋል።።

እንደ ዶክተር ተስፋዬ ገለጻ፤ ዛሬ የተደረገው  የስንዴ ምርጥ ዘር ድጋፍ  በሄክታር  እስከ 60 ኩንታል ምርት የሚሰጥ ነው።

ዩኒቨርሲቲው በሚያደርገው የስንዴ ምርጥ ዘር ድጋፍ በምስራቅ ሐረርጌ ዞን  25ሺህ ሄክታር መሬትን በመስኖ ስንዴ ማልማት ተችሏል ያሉት ደግሞ የዞኑ  ግብርና ጽህፈት ቤት ሃላፊ አቶ ጌታሁን ንጋቱ ናቸው።

ዛሬው ደግሞ በዞኑ ስምንት ወረዳዎች ተጠቃሚ የሚያደርግ 1ሺህ ኩንታል ምርጥ የስንዴ ዘርን ድጋፍ መደረጉን አረጋግጠዋል።

ዩኒቨርሲቲው ባለፈው ዓመትም  3ሺ 400 ኩንታል ምርጥ የስንዴ ምርጥ ዘር ለአርሶ አደሩ ድጋፍ ማድረጉንም አስታውሰዋል።

የሐረማያ ወረዳ የግብርና ጽህፈት ቤት ሃላፊ አቶ ሽኩሪ መሀመድ በበኩላቸው፤ ዩኒቨርሲቲው በምርምር የተገኙ ምርጥ የሰብል ዝርያዎችን ለአካባቢውን አርሶ አደሮች በማሰራጨት ምርታማነትን ለማሳደግ ድጋፍ እየደረገ መሆኑን ገልጸዋል።

ዩኒቨርሲቲው  ባለፈው ዓመት በጋ ወራት ለወረዳው አርሶ አደር ምርጥ የስንዴ ዝርያን በማሰራጨት አርሶ አደሩ  እስከ 69 ኩንታል በሄክታር እንዲያገኝ አስችሏል ብለዋል።

ዘንድሮም በወረዳው በ500 ሄክታር  መሬት ላይ ስንዴን በመስኖ ለማልማት ዝግጅት መጠናቀቁንም ጠቁመዋል።

በምሰራቅ ሐረርጌ ዞን ዘንድሮ በጋ ወራት 25ሺ ሄክታር መሬትን  ስንዴ በመስኖ  ለማልማት መታቀዱ ተገልጿል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም