የሰላም ስምምነቱ የዜጎችን ዘላቂ ሰላም በማስጠበቅ በጋራ ለመበልጸግ የሚያስችል መሰረት የጣለ ነው- የአማራ ክልል መንግስት

224

ባህር ዳር ጥቅምት 28/2015 (ኢዜአ) በደቡብ አፍሪካ ፕሪቶሪያ የተደረገው የሰላም ስምምነት የዜጎችን ዘላቂ ሰላም በማስጠበቅ በጋራ ለመበልጸግ የሚያስችል መሰረት የጣለ መሆኑን የአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት አስታወቀ።

የክልሉ መንግስት ዛሬ ማምሻውን በወቅታዊ ጉዳይ ላይ ባወጣው መግለጫ እንዳስታወቀው የሰላም ስምምነቱ  የታለመለትን ዘላቂ ሰላም እንዲያመጣ ለተግባራዊነቱ የሚጠበቅበትን ሁሉ ለመወጣት ከወዲሁ ዝግጁ መሆኑን አስታውቋል።

"በደቡብ አፍሪካ ፕሪቶሪያ የተደረገው የሰላም ስምምነት ለሁለቱም ወንድማማች ህዝቦች ዳግም ትንሳኤ ወሳኝ ከመሆኑም በላይ ከቂምና ከቁርሾ የዘለለ ህብረትን፣ አንድነትንና የጋራ እሴትን በጋራ የምንገነባበትን መሰረት ይጥላል" ብሏል  በመግለጫው።

"የደቡብ አፍሪካው የሰላም ስምምነት እውን መሆን እንደ ክልል መንግስት የምንፈልገውና አጥብቀን ስንመኘው የነበረ መሆኑን  እየገለጽን ለተግባራዊነቱ የሚጠበቅብንን ሁሉ ለመወጣት ዝግጁ መሆናችንን አበክረን እንገልፃለን" ሲል አመልክቷል።

"ስለሆነም በጦርነቱ ምክንያት የወደመውን የሕዝብ ሀብት መልሶ ለመተካትና  የዘላቂ መልሶ ግንባታ ሥራው እንዲፋጠን ለማድረግ ከምንጊዜውም በላይ የተፈጠረውን የሰላም አየር ተጠቅመን መረባረብ ይኖርብናል" ሲል ገልጿል።

"ሰላም ወዳድ የሆነው ሕዝባችን የሰላም ስምምነቱ ለአገር ሉዓላዊነትና ለግዛት አንድነት ወሳኝ መሆኑን በመረዳት ከደረሰብን ጉዳት ለማገገምና ዘላቂ ሰላምን ለማስፈን በሚደረገው ጥረት እንደወትሮው ሁሉ ከክልሉ መንግስት ጎን በመቆም አስፈላጊውን ሁሉ እንድታደርጉ ጥሪያችንን እናስተላልፋለን" ሲል የክልሉ መንግስት በመግለጫው አስታውቋል ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም