በስድስት ከተሞች የሚካሄዱ የኤሌክትሪክ ኔትወርክ ማሻሻያ ስራዎች አፈጻጸም ከ70 በመቶ በላይ ደርሷል- የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት

152

አዲስ አበባ /ኢዜአ/ ጥቅምት 28/2015 በኢትዮጵያ በተመረጡ ስድስት ከተሞች የሚካሄዱ ኤሌክትሪክ ኔትወርክ ማሻሻያ ስራዎች አፈጻጸም ከ70 በመቶ በላይ መድረሱን የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት አስታወቀ።

አገልግሎቱን ለማሻሻል እና የህብረተሰቡን እርካታ ለመጨመር የሚያግዝ የውይይት ፎረም  በአዲስ አበባ ተካሂዷል።

በፎረሙ የፌደራልና ክልል ህዝብ ግንኙነት ባለሙያዎች፣ አመራሮችና ከተለያዩ መገናኛ ብዙሃን የተውጣጡ ጋዜጠኞች የተሳተፉ ሲሆን፤ በመድረኩም አገልግሎቱ በቀጣይ ሶስት ዓመታት በሚተገብረው ስትራቴጂክ እቅድ ላይ ውይይት ተደርጓል፡፡

የአገልግሎቱ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ሽፈራው ተሊላ፤ አገልግሎቱ የህዝቡን ጥያቄዎች ለመመለስ ተከልሶ በአዲስ መልክ የተዘጋጀ የሦስት ዓመት ስትራቴጂ ነው ብለዋል።

ስትራቴጂው ተቋሙ የሚገጥመውን የፋይናንስ ችግር፣ የማከፋፈያ ኔትወርክ ልማትና ቴክኖሎጂ ላይ ትኩረት ያደረገ መሆኑን አብራርተዋል።  

ከዋና ግሪድ ርቀት ላይ ያሉ አካባቢዎችን የኃይል ተጠቃሚ ለማድረግ ኤሌክትሪክ እንዲያገኙ የተለያዩ ተግባራት በመከናወን ላይ እንደሚገኙ አንስተዋል።

የኤሌክትሪክ መሰረተ ልማቶች ላይ የሚፈጸም ዝርፊያና ውድመት፣ አንዳንድ ደንበኞች የፍጆታ ሂሳባቸውን በወቅቱ አለመክፈላቸውና ቅንጅታዊ አሰራር በተገቢው መልኩ አለመተግበራቸው እያጋጠሙ ካሉ ችግሮች መካከል ይገኙበታል ብለዋል።       

የመልካም አስተዳደር ችግሮች በሚስተዋልባቸው የአገልግሎቱ ሰራተኞች ላይም ማስረጃን መሰረት ባደረገ መልኩ ህጋዊ እርምጃ እየተወሰደባቸው መሆኑንም ገልጸዋል።

በኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት የለውጥና መልካም አስተዳደር ዳይሬክተር እሱባለዉ ጤናው በበኩላቸው አገልግሎቱ ላይ የሚከሰቱ መቆራረጦችን በጊዚያዊነት ለመፍታት የጥገና ስራዎች እየተከናወኑ ይገኛሉ፡፡    

በዚህም በአዲስ አበባ  የመጀመሪያው ምዕራፍ የኔትወርክ ማሻሻያ ስራዎች ተጠናቀው ቀጣይ ስራዎች ተጀምረዋል ብለዋል፡፡      

ተቋሙ በክልሎች ደግሞ የመካከለኛ  ቮልቴጅ፣ትራንፎርመሮች እና ዝቅተኛ መስመር ማሻሻያ ስራ እየተከናወነ መሆኑንም አንስተዋል፡፡

የማሻሻያ ስራዎችም በጎንደር፣ ሻሸመኔ፣ ደብረማርቆስ፣ ወላይታ ሶዶ፣ ሐረርና ኮምበልቻ ከተማ እየተካሄደ ሲሆን አፈጻጸሙ ከ70 በመቶ በላይ መድረሱ ተገልጿል።    

በቀጣይም በአስር ከተሞች ላይ በተመሳሳይ የኔትወርክ ማሻሻያው እንደሚካሄድም ጠቁመዋል።

ከውይይቱ ተሳታፊዎች መካከል ከኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን የተወከሉት አቶ ሞላልኝ መለሰ እንዳሉት፤ ተቋሙ ከሚያከናውናቸው የመሰረተ ልማት ማሻሻያዎች እና አዲስ ለሚገነባው ከፍተኛ የውጭ ምንዛሬ የሚጠይቅ በመሆኑ በዚህ ላይ የበለጠ ሊሰራ ይገባል።

ሌላው አስተያየት ሰጪ የትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ሚኒስቴር የህዝብ ግንኙነትና ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ሥራ አስፈጻሚ ታጠቅ ነጋሽ በበኩላቸው ሚኒስቴሩ በዘርፉ የግል ባለሃብቶችን በማሳተፍ የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎችን በስፋት ስራ ላይ ለማዋል እየሰራ ነው።  

ይህንን ለማካሄድ ደግሞ በቂ የኤሌክትሪክ አቅርቦት አስፈላጊ መሆኑን ጠቅሰው በተለይ በሚቀጥሉት ሦስት ዓመታት ገቢራዊ ለማድረግ የተዘጋጀው ስትራቴጂያዊ ዕቅድ ፋይዳው ከፍ ያለ እንደሚሆን ያላቸውን እምነት ገልጸዋል፡፡  

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም