ገቢን አሟጦ በመሰብሰብ የህዝብን የልማት ተጠቃሚነትና የሰላም ግንባታን ለማረጋገጥ ይሰራል- ዶክተር ይልቃል ከፋለ

100

ባህር ዳር (ኢዜአ) ጥቅምት 28/2015 በክልሉ ኢኮኖሚው የሚያመነጨውን ገቢ አሟጦ በመሰብሰብ የህዝብን የልማት ተጠቃሚነትና የሰላም ግንባታን ለማረጋገጥ በልዩ ትኩረት ይሰራል ሲሉ የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ዶክተር ይልቃል ከፋለ ገለፁ።

የክልሉ ገቢዎች ቢሮ የ2014 ዓ.ም የእቅድ አፈፃፀም እውቅናና የ2015 ዓ.ም እቅድ ንቅናቄ መድረክ ዛሬ በባህር ዳር ከተማ ተካሂዷል።

ርዕሰ መስተዳድሩ ዶክተር ይልቃል ከፋለ በንቅናቄ መድረኩ ላይ እንዳሉት ገቢ ለአንድ ሀገር መንግስት የደም ስር ነው።

በክልሉ ሰላምን ከማረጋገጥ ጎን ለጎን ለሁለንተናዊ ልማት ትኩረት ተሰጥቶ በመሰራቱ ለቀጣይ የለውጥ ምዕራፍ መሰረት መጣሉን ገልጸዋል።

በእዚህም ምስጉን ግብር ከፋዮች፣ የዘርፉ አመራሮችና ባለሙያዎች ለክልሉ ልማትና ሰላም አስፈላጊውን ሀብት በማመንጨት የማይተካ ሚና መጫወታቸውን ተናግረዋል።

በተያዘው በጀት ዓመትም በክልሉ ኢኮኖሚው የሚያመነጨውን ገቢ አሟጦ በመሰብሰብ የህዝብን የልማት ተጠቃሚነትና የሰላም ግንባታን ለማረጋገጥ በትኩረት እንደሚሰራ ርዕሰ መስተዳድሩ ገልጸዋል።

በዛሬው እለት እውቅና የሚያገኙ አካላት በቀጣይ በግብር አሰባሰብ ሥራው በግንባር ቀደምነት እንዲንቀሳቀሱ ሽልማቱ ብርታት እንደሚሆናቸውም ተናግረዋል።

የክልሉ ገቢዎች ቢሮ ሃላፊ ዶክተር ፀጋ ጥበቡ በበኩላቸው "በ2014 ዓ.ም ከ30 ቢሊዮን በላይ ለመሰብሰብ ታቅዶ በተደረገ ጥረት ከ27 ቢሊዮን ብር በላይ ተሰብስቧል" ብለዋል።

የተሰበሰበው ገቢ በዓመቱ በአብዛኛው በክልሉ ከነበረው የፀጥታ ችግር አንፃር ሲታይ አበረታች የሚባል መሆኑንም ገልጸዋል።  

በተያዘው ዓመት 42 ነጥብ 8 ቢሊዮን ብር ገቢ ለመሰብሰብ ታቅዶ እየተሰራ መሆኑን ጠቁመው፣ የእውቅና ስነ ስርአቱም እቅዱን ለማሳካት ያበረታታል ብለዋል።

በመድረኩ ላይ 49 ምስጉን ግብር ከፋይ ድርጅቶችን ጨምሮ የክልል ቢሮዎች፣ ወረዳዎች፣ መገናኛ ብዙሀን፣ የዘርፉ ባለሙያዎች እና ሌሎች አካላት እውቅና ተሰጥቷቸዋል።

በመድረኩ ላይ የክልሉ ከፍተኛ አመራሮች፣ የሁሉም ዞኖች አስተዳዳሪዎች፡ ምስጉን ግብር ከፋዮችና ሌሎች ጉዳዩ የሚመለከታቸው አካላት ተሳትፈዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም