የዚህ ዓመት የዓለም ሠላም ቀን መታሰቢያነቱ ለኢትዮጵያ እና ኤርትራ እንደሚገባ ተገለፀ

144
አዲስ አበባ መስከረም 15/2011 የዚህ ዓመት የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የሠላም ቀን መታሰቢያነቱ ለኢትዮጵያ እና ኤርትራ ሊሆን ይገባል ተባለ። እንደ አውሮጳውያን አቆጣጠር በ2011 የሠላም ኖቤል ተሸላሚ የሆኑት ላይቤሪያዊቷ ሌይማህ ግቦዌ የዘንድሮው የተባበሩት መንግስታት የሠላም ቀን መታሰቢያነቱ ለኢትዮጵያ እና ኤርትራ መሆን አለበት ብለዋል። ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ እና የኤርትራው ፕሬዝዳንት ኢሳይያስ አፈወርቂ ከ20 ዓመታት በላይ በአገራቱ መካከል የነበረው አለመግባባት እንዲወገድ ላበረከቱት ከፍተኛ አስተዋጽኦ የዚህ ዓመት የዓለም ሠላም ቀን መታሰቢያነቱ ለሁለቱ አገሮች እንደሚገባ ተናግረዋል። የቀድሞዋ የላይቤሪያ መሪ የነበሩት ኤለን ጆንሰን ሰርሊፍ እና የየመን የሰብአዊ መብት ተሟጋች ከነበሩት ታዋኒ ካርማን ተርታ እንደ አውሮጳውያን አቆጣጠር በ2011 የሠላም ኖቤል ተሸላሚ የሆኑት ሌይማህ ግቦዌ በሁለቱ አገራት መካከል የሰፈነው ሰላም ለዓለም ተምሳሌት እንደሚሆን እና ሌሎች አገራት ሊማሩበት እንደሚችሉ በአጽንኦት ገልፀዋል። የዓለም ዓቀፍ የሠላም ቀን በተባበሩት መንግስታት ድርጅት በየዓመቱ መስከረም የሚከበር በዓል ነው። ዕለቱ እንደ አውሮጳውያን አቆጣጠር ከ1981 አንስቶ መከበር የጀመረ ሲሆን የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ከ2011 ጀምሮ ከሁከትና ከጥይት ድምጽ በጸዳ መልኩ እንዲከበር በወሰነው መሰረት ዕለቱ ሠላምን በሚሰብኩ ነገሮች ይከበራል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም