ኢትዮጵያ ፈተናዎችን ተቋቁማ በማለፍ ለወዳጆቿና ጎረቤት አገራት ተስፋ ሆናለች-አምባሳደር ብርቱካን አያኖ

118

አዲስ አበባ (ኢዜአ) ጥቅምት 28 ቀን 2015 ኢትዮጵያ ፈተናዎችን ተቋቁማ በማለፍ ለወዳጆቿና ጎረቤት አገራት ተስፋ ሆናለች ሲሉ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዲኤታ አምባሳደር ብርቱካን አያኖ ገለጹ።

ሚኒስትር ዲኤታዋ ይህን የተናገሩት የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር "እኔ ለሀገሬ" በሚል መሪ ሃሳብ ለቀጣዮቹ 20 ቀናት የሚቆይ ስልጠና ለዲፕሎማቶች መስጠት በጀመረበት መድረክ ላይ ተገኝተው የመክፈቻ ንግግር ባደረጉበት ወቅት ነው።

አክለውም ከፍተኛ ጫና በበዛበት የባለፉት የለውጥ ዓመታት ውጤታማ የዲፕሎማሲ ስራ መከናወኑንና ኢትዮጵያም ፈተናዎችን ተቋቁማ በማለፍ ለወዳጆቿና ጎረቤት አገራት ተስፋ መሆኗን አሳይታለች ብለዋል።

ዲፕሎማቶች ኢትዮጵያ ያለችበትን ወቅታዊ ሁኔታ ከግምት ውስጥ በማስገባት ለዲጂታል ዲፕሎማሲ ልዩ ትኩረት ሰጥተው መስራት እንደሚገባቸውም በማሳሰብ።

ሱሉልታ በሚገኘው የአፍሪካ አመራር ልህቀት አካዳሚ በተጀመረው ስልጠና ኢኮኖሚያዊ፣ ወታደራዊ፣ ፓለቲካዊ፣ ቀጠናዊና ዓለም አቀፋዊ ጉዳዮች እንደሚዳሰሱ ተገልጿል።

የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብን ጨምሮ ሌሎች ግዙፍ ፕሮጀክቶች ግንባታ ውጤታማ በሆነ መልኩ ስራዎች እየተከናወኑ እንደሚገኝም ጭምረው ገልጸዋል።

ብዝሃነትን መሰረት ባደረገ መልኩ እየተሰሩ ባሉ የዲፕሎማሲ ስራዎች ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ጥቅም መከበር የሚተጉ ወጣት ዲፕሎማቶችን ማፍራት እየተቻለ መሆኑንም አመልክተዋል።

ዲፕሎማቶቹ ኢትዮጵያ አሁን ያለችበትን ሁኔታ በመገንዘብ ሰፊ የዲጂታል ዲፕሎማሲ ማከናወንና አገሪቷ በቀጠናው እያስመዘገበች የሚገኘውን ተስፋ ሰጪ ውጤት ማሳየት ይጠበቅባቸዋል ነው ያሉት አምባሳደር ብርቱካን።

የአፍሪካ አመራር ልህቀት አካዳሚ ፕሬዚደንት ዶክተር ምህረት ደበበ አካዳሚው ለኢትዮጵያ ጉልህ ጠቀሜታ የሚሰጡ ስልጠናዎችን እየሰጠ እንደሚገኝ ገልጸዋል።

በወሳኝ ወቅት ላይ የምትገኘው ኢትዮጵያ ችግርችን በሰላም ለመቋጨት የተደረሰው የሰላም ስምምነት በጎ የሚባል ነው ብለዋል።

በዲፕሎማሲው ዘርፍ የተሰማሩ ዲፕሎማቶችም ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ጥቅም መከበር አበክረው ሊሰሩ እንደሚገባ አመልክተዋል።

የስልጠናው ተሳታፊ ዲፕሎማቶችም ተለዋዋጭና ኢ-ተገማችነቱ እየጨመረ የመጣውን የዓለም ሁኔታ የሚመጥን ግንዛቤ ለመያዝ ስልጠናው ጠቀሜታ እንዳለው ተናግረዋል።

በስልጠናው የኢትዮጵያን ሉዓላዊ ክብርና ጥቅም ማስጠበቅ የሚያስችል ግንዛቤ በመያዝ ለተሻለ ግብ የሚያነሳሳ እንደሆነም ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም