የወዳጅነት ፓርክ ቁጥር ሁለት እጅግ ውብ የሆነና መንፈስን የሚያድስ የመዝናኛ ስፍራ ሆኖ አግኝተነዋል - ጎብኚዎች

847

ጥቅምት 27 ቀን 2015/ኢዜአ/ በመዲናዋ የተከፈተው የወዳጅነት ፓርክ ቁጥር ሁለት እጅግ ውብ የሆነና መንፈስን የሚያድስ የመዝናኛ ስፍራ ሆኖ አግኝተነዋል ሲሉ ከተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች የመጡ ጎብኚዎች ገለጹ።

በአዲስ አበባ የተገነቡት አዳዲስ ፓርኮች የኢትዮጵያን ሕብረ ብሔራዊነት የሚያሳዩና በውስጣቸው በርካታ የተፈጥሮ እጽዋትን፣ እንስሳትንና የልጆች መጫወቻ ቦታዎችን ያካተቱ ናቸው።

በአዲስ አበባ ከተገነቡት እንጦጦ፣ ወዳጅነት ፓርክ ብሎም ከአንድነት ፓርክ ቀጥሎ በተለይም ለታዳጊዎችና ልጆች ትኩረት ሰጥቶ የተገነባው የወዳጅነት ፓርክ ሁለተኛው ፕሮጀክት አገልግሎት መስጠት ከጀመረ ጥቂት ቀናት አስቆጥሯል።

ፓርኩን መርቀው የከፈቱት ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ በወቅቱ "ህፃናትና ወጣቶች አካላቸውና አዕምሯቸው የሚዳብርበት ስፍራ በመሃል ከተማ ተገንብቷል፤ እንደ ወዳጅነት ፓርክ ምዕራፍ ሁለት ፕሮጀክት በየክልሉ ለህፃናት የሚሆኑ ሥፍራዎች ያስፈልጋሉ" ማለታቸው ይታወሳል።

ፓርኩ ተመርቆ ለህዝብ ክፍት ከሆነበት እለት አንስቶ በሺዎች የሚቆጠሩ ተማሪዎች፣ ወላጆች፣ ወጣቶችና ጎልማሶች ስፍራውን እየጎበኙት ይገኛል።

ኢዜአ በስፍራው በመገኘት ያነጋገራቸው ጎብኚዎች እንደገለጹት፣ ፓርኩ ለመዲናዋ ተጨማሪ ውበት በመስጠት ማራኪ ገጽታ አላብሷታል።

ፓርኩ ህፃናት በአንድ ቦታ ሁሉንም አይነት መጫወቻ የሚያገኙበት ጥሩ የመዝናኛ አማራጭ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

መዝናኛው ወጣቶችና ጎልማሶች ከጓደኞቻቸውና ከልጆቻቸው ጋር አረፍ ብለው የሚያወጉበት፣ ምቾት የሚሰጥና ቀልብን የሚስብ መሆኑንም ገልጸዋል።

ከዚህ ቀደም በመዲናዋ በዚህ ልክ የልጆች መጫወቻና መዝናኛ ስፍራ እንዳልነበር በመጥቀስ እንዲህ ያሉ የመዝናኛ ስፍራዎች ትውልዱን በስነ ምግባር ለመገንባት ትልቅ ፋይዳ እንዳላቸው አስረድተዋል።

ስፍራው የተለየና ከመዝናኛነት ባለፈ ለብዙ አገልግሎቶች የሚውል መሆኑንም መመልከታቸውንም ተናግረዋል።

በመዲናዋ ያለውን የመዝናኛ ቦታ እጥረት በመረዳት ስፍራውን በዚህ ልክ በማስዋብ ለህዝብ አገልግሎት እንዲሰጥ መደረጉ እንዳስደሰታቸው ተናግረዋል።

ፓርኩ ለህጻናትና ለተማሪዎች እጅግ ምቹ  የመዝናኛ ስፍራ መሆኑን በመጥቀስ ተግባሩ መንግስት ትውልዱን በስነ ምግባር ለመገንባት የጀመረውን ጥረት ያሳያል ብለዋል።

እንደዚህ አይነት ማራኪ ስፍራዎች ጤናማ ትውልድ ለመፍጠር እንደሚያግዙም ተናግረዋል።

ፓርኩ የአገሪቱ የነገ ተስፋ ለሆኑ ህፃናት ቅድሚያ በመስጠት የተገነባ ትልቅ ሀገራዊ ፕሮጀክት መሆኑን ነው የተናገሩት።

ስፍራውን ያላዩ የመዲናዋ ነዋሪዎችና በአገሪቱ የተለያዩ ክልሎች የሚኖሩ ዜጎች እንዲጎበኙትም መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።

ጠቅላይ ሚስትር ዐቢይ አህመድ በአዲስ አበባ ከተማ እንጦጦ ፓርክን ጨምሮ የተለያዩ ቦታዎችን ምቹ፣ መንፈስን የሚያድሱ የመዝናኛና የስፖርት ቦታዎችን በመገንባት ለተጠቃሚዎች ክፍት ማድረጋቸው ይታወሳል፡፡

አሁን ላይ ከአዲስ አበባ ውጭ ግዙፍ የሆኑትን  የጎርጎራ፣የኮይሻና ወንጪ ሀይቅ አካባቢዎችን ተመራጭ የቱሪስት መድረሻ ለማድረግ የሚያስችል ፕሮጀክቶች ይፋ በማድረግ ግንባታቸው እየተከናወነ እንደሆነም ይታወቃል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም